የኮሮና ወረርሽኝ በአዕምሮ ጤና ላይ ከሚያስከትለው ጉዳት ራስን መጠበቅ ይገባል

49

ሰኔ 21/2012(ኢዜአ) የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በአዕምሮ ጤና ላይ ከሚያስከት ለው ጉዳት ራስን መጠበቅ እንደሚገባ የሥነ-አዕምሮ ባለሙያዎች አሳሰቡ።

የሥነ- አዕምሮ ባለሙያዋ ወይዘሮ ትዝታ ሰዴቻ እንደሚሉት ዜጎች አውቀውም ይሁን ሳያውቁት በአኗኗር ዘይቤያቸው መቀየርና ሌሎች ተዛማች  ችግሮች  ለአዕምሮ ሕመም ይዳረጋሉ።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ   ለአዕምሮ  ሕመም የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ጥናቶች አመላክተዋል።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በኢትዮጵያም የአዕምሮ ጤና እክል ያጋጠማቸው ዜጎች ቁጥር በሶስት እጥፍ አድጓል ነው የሚሉት።

ኮቪድ-19 በባህሪው ቀድሞ ከነበረን ወደ አዲስ የአኗኗር  ዘይቤ ስለሚወስድ  ሰዎች አዲሱን ዘይቤ ለመላመድ በሚያደርጉት ጥረት ለጭንቀት  ይዳረጋሉ።

እኔና ቤተሰቤ በወረርሽኙ ብንጠቃስ፣ የኢኮኖሚ  ጫና ቢደርስብንስ የሚሉና  በተጓዳኝ ሕመሞች ሳቢያ በወረርሽኙ ሊጠቁ ይችላሉ ተብለው ከሚጠቀሱ መካከል ሲሆኑ ለጭንቀት ይዳረጋሉ።

በዚህ ሳቢያ ዕንቅልፍ ማጣት፣ የሰውነት መዛል፣ የሕመም ስሜቶች  በተደጋጋሚ መሰማት፣ ሕመሞችን የማስተናገድ፣ ግራ የመጋባት፣  የመነጫነጭና  የትኩረት ማጣት ችግሮች ይከሰታሉ።

ሰዎች  ረጅም ጊዜያቸውን ስለ በሽታው መረጃ በማነፍነፍ ወይም  ጨርሶ  በመሸሽ  ላይ እያተኮሩ ከሆነም ለአዕምሮ ሕመም  ሊዳረጉ እንደሚችሉ ማወቅ አለባቸው ነው ያሉት ባለሙያዋ።

ችግሮችን ለመቆጣጠር መፍትሄው በእጃችን ነው ያሉት ወይዘሮ ትዝታ በቅድሚያ ለአካላዊ ሰውነታችን የምንሰጠውን ያህል ለአዕምሯችንም ትኩረት መስጠት ይጠበቅብናል ብለዋል።

ቤተሰብ ለዚህ ችግር እንዳይዳረግ በቤት ውስጥ ውይይትና ግልፅነትን ማስፈን፣ ራስን መቆጣጠርና መምራት መቻልን ማዳበር እንደሚገባም መክረዋል።

በተጨማሪም ለተከሰተው ወረርሽኝ እውቅና ሰጥቶ መከላከል ላይ ማተኮርና 'የቤታችንን ዓለም በአግባቡ መቆጠጠር ነው' ብለዋል።

የወረርሽኙን የተወሰነ መረጃ ከታማኝ ምንጮች ብቻ  በመጠቀምም  ከሚገ ጥም  የአዕምሮ ጭንቀት መላቀቅ ይቻላል ብለዋል።

አንድ ሰው ጤነኛ የሚባለው አካላዊና ማኅበራዊ እንዲሁም የስራ ሕይወቱ ጤናማ ሲሆን  በመሆኑ ለአዕምሮ ትኩረት መስጠት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

መንግስትም መረጃዎችን ለሕዝቡ በጥራትና በፍጥነት ማድረስ፣ የወጡ መመሪያዎች በአግባቡ መተግበራቸውን መከታታልና የተሳሳቱና ለጭንቀት የሚዳርጉ መረጃዎችን በሚያወጡ ላይ እርምጃ መውሰድ ይጠበቅበታል  ብለዋል።

ወላጆች ሕጻናት የችግሩ ሰላባ እንዳይሆኑ  መከታተልና በቂ  መረጃ በመስጠት  ሊያስተምሩ ይገባልም ብለዋል ባለሙያዋ።

ሌላው የሥነ-ልቦና ባለሙያው አቶ አንተነህ መሃሪም ሰዎች ችግሮችን በውይይት መፍታትና አዲስ ለሆነው የአኗኗር ዘይቤ መፍትሄ በራሳቸው ማበጀት ይጠበቅባቸዋል ይላሉ።

በአዕምሮ ሕመም ተይዣለሁ ብሎ ሲያስብ የመደበር፣ የመከፋት፣ ስጋትና ጭንቀት ሲኖር ፈጥኖ ወደ ሕክምና ተቋም መሄድ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በተለይ ቀድሞ የአዕምሮ ሕመም ያለባቸው ሰዎች በወረርሽኙ ሳቢያ ችግር ሊገጥማቸው ስለሚችል የበለጠ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም