ኢትዮጵያ በአህጉሩ የህገወጥ መድሀኒት ጉዳትን ለመከላከል የሚያስችል ቅንጅት ለመፍጠር እየሰራች ነው

96
አዲስ አበባ ሀምሌ 2/2010  ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉር ህገወጥ መድሀኒት እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመከላከል የሚያስችል ቅንጅት ለመፍጠር እየሰራች መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶክተር አሚር አማን ገለጹ። ለሁለት ቀናት የሚቆየው የምስራቅ አፍሪካ የጤና ጥበቃ ፌዴሬሽን ሰባተኛው ዓመታዊ ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ ዛሬ ተጀምሯል። በመክፈቻው የተገኙት ዶክተር አሚር ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ያስመዘገበችውን ስኬትና ያጋጠማትን ፈተና ለኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች አጋርተዋል። የአገሪቱን የጤና ዘርፍ ለማዘመን የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት በርካታ ስራ የተሰራ ቢሆንም የጤና ባለሙያዎች ጥራት ጉዳይ በህብረተሰቡ፣ በመንግስትና በዘርፉ ባለሙያዎች ጥያቄ የሚነሳበት እንደሆነ ገልጸዋል። የጤና ባለሙያዎችን በጥራት አሰልጥኖ ለማሰማራት ሚኒስቴሩ ከምስራቅ አፍሪካ የጤና ጥበቃ ፌዴሬሽን ጋር በመተጋገዝ የሚሰራ መሆኑን ዶክተር አሚር ጠቁመዋል። ህገወጥ መድሃኒት በአህጉር ደረጃ ፈታኝ የሆነ ችግር በመሆኑ ከፍተኛ ትብብር የሚጠይቅ የጋራ ችግር እንደሆነ የገለጹት ዶክተር አሚር፤ የህገወጥ መድሀኒት ችግር “መፈወስ አለመቻል ብቻ ሳይሆን የተላመደ መድሀኒት በማምጣት በአገርና በዓለም ደረጃ ከፍተኛ ስጋት ነው” ብለዋል። ችግሩን ለመፍታት በአፍሪካ ደረጃ የጋራ የህገወጥ መድሀኒቶች ቁጥጥር ስርዓት ለመዘርጋት ኢትዮጵያ ያላትን መነሻ ዕቅድ ለአፍሪካ ህብረትና ለዓለም የጤና ድርጅት ማቅረቧን ጠቁመዋል። በምስራቅ አፍሪካ ደረጃ ህገወጥ መድሃኒትን ቁጥጥር ለማድረግ የሚያስችል የምግብና የመድሃኒት ባለስልጣን በጋራ ለማቋቋም ከምስራቅ አፍሪካ የጤና ጥበቃ ፌዴሬሽን ጋር በትብብር እንደሚሰራ አመልክተዋል። ይሄን ተከትሎ ከተያዘው የሐምሌ ወር ጀምሮ የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ስያሜው 'ምግብና መድሀኒት ባለስልጣን' በሚል ተቀይሮ አገልግሎት እንዲሰጥ የሚደረግ መሆኑን ጠቁመዋል። የምስራቅ አፍሪካ የጤና ጥበቃ ፌዴሬሽን ሊቀመንበር ወይዘሮ ዘላለም ፍስሃ በበኩላቸው ፌዴሬሽኑ በምስራቅ አፍሪካ የጤና ዘርፍ ተሞክሮዎች በማስፋትና የግሉን የጤና ዘርፉ ለማሳደግ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል። በአካባቢው የሚታየውን የጤና ዘርፍ ችግር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመወያየት መፍትሔ የመፈለግ ሥራ እንደሚሰራ ገልፀዋል። በአፍሪካ ቀንድ ተዘዋውረው መስራታቸውን የገለፁት ፕሮፌሰር ክሃማ ሮጎ በኢትዮጵያ ጥሩ የጤና ፖሊሲና ለቢዝነስ ክፍት የሆነ ሁኔታ መኖሩን መታዘባቸውን ገልጸው በምስራቅ አፍሪካ የመድሀኒት ኢንዱስትሪዎችን ለማስፋፋት በኢትዮጵያ የተጀመረው ሥራ ጠቃሚ እንደሆነ ተናግረዋል። ይሁን እንጂ በጤና ባለሙያዎች ጥራት ያለው ጉድለትና የባለሙያዎች በክፍያ ደስተኛ አለመሆን ካልተፈታ ለውጥ ለማምጣት አስቸጋሪ መሆኑን ገልጸዋል። ዛሬ በተጀመረው የፌዴሬሽኑ ጉባኤ ኢትዮጰያን ጨምሮ በአፍሪካ ቀንድ አገሮች በጤና ዘርፉ የተገኙ ስኬቶችና ተግዳሮች ላይ ውይይት ይደረግባቸዋል። ፌዴሬሽኑ በፈረንጆች በ2012 የተመሰረተ ሲሆን ኢትዮጵያ፣ ኡጋንዳ፣ ኬንያ፣ ታንዛንያ፣ ሩዋንዳ፣ ብሩንዲ እና ደቡብ ሱዳንን በአባልነት ያቀፈ ነው፤ፌዴሬሽኑ የጤና የግል ዘርፍ ተሳትፎን ለማሳደግ ትኩረት ያደረገ ነው።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም