በአሶሳ ከተማ ለረጅም ዓመታት አለአግባብ ታጥሮ የተቀመጠ 40 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ለመንግስት ገቢ ተደረገ

46

አሶሳ ፣ ሰኔ 21 / 2012 ዓ.ም (ኢዜአ )  የአሶሳ ከተማ አስተዳደር ከሃገራዊ ለውጡ በፊት ከማዕከላዊ መንግስት በጫና በኢንቨስትመንት ስም ለግለሰቦች ተላልፎ ለረጅም ዓመታት ሳይለማ ታጥሮ የተቀመጠ 40 ሺህ ካሬ ሜትር የከተማ ቦታ እንዲመለስ ማድረጉ ገለፀ ።

የአስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ኡመር መሃመድ ለኢዜአ እንደተናገሩት መሬቱን ሰሞኑን እንዲመለስ የተደረገው በከፍተኛ እና መካከለኛ ኢንቨስትመንት ሽፋን የተወሰደው መሬት በ25 ግለሰቦች ለረጅም ዓመታት ሳይለማ ታጥሮ ተቀምጦ የነበረ ነው ።

ግለሰቦቹ መሬቱን በኢንቨስትመንት ስም  መሬቱን የተረከቡት ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ እንደነበር ከንቲባው አስረድተዋል፡፡

ከባለሃብቶቹ መካከል 14ቱ የተረከቡትን ከ40 ሺህ 027 ካሬ ሜትር ለዓመታት አጥረው ከማስቀመጥ ውጪ ምንም ባለመስራታቸው የያዙት ቦታ ተነጥቆ ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ ተደርጓል ፡፡

ሌሎች 10 ባለሀብሃቶች ስራ ጀምረው ያቆሙ አሉ ያሉት አቶ ኡመር በአንድ ወር ውስጥ ወደ ስራ እንዲገቡ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል፡፡

በተቀመጠላቸው ጊዜ ሥራ ካልጀመሩ አስተዳደሩ የያዙትን መሬት እንደሚነጥቃቸው ከንቲባው አስታውቀዋል፡፡

ከሃገራዊ ለውጡ በፊት ለሆቴል እና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውል የኢንቨስትመንት መሬት ለግለሰቦቹ እንዲሰጥ አስተዳደሩ ከማዕከላዊ መንግስት ጫና ሲደረግበት እንደነበር አቶ ኡመር አስታውሰዋል፡፡

ለሃገር ልማት የባለሃብቱ ሚና ወሳኝ እንደሆነ አስተዳደሩ ያምናል ያሉት ከንቲባው በከተማው ወሳኝ የሆኑ ቦታዎች ለረጅም ዓመታት ሳያለሙ ያስቀመጡ ግለሰቦች ህዝብ እና መንግስትን በሚሊዮኖች የሚገመት ገቢ እንዲያጡ ምክንያት መሆናቸውን ገልፀዋል ።

ታጥሮ የተቀመጠው መሬት ቢለማ ኖሮ ለበርካታ ወገኖች የሥራ እድል ምንጭ ሆኖ ያገለግል ነበር በማለት ጉዳቱ ዘርፈ ብዙ መሆኑን አስረድተዋል ።

አስተዳደሩ ችግሩ በዚህ መቀጠል እንደሌለበት ቁርጠኛ አቋም አለው ያሉት ከንቲባው ውስን ሃብት የሆነውን የከተማ መሬት በአግባቡ ለማልማት ተግባራዊ ስራ መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡

የሊዝ አዋጁ መሬት በወሰዱት ልክ የማያለሙ ባለሃብቶች ባደረሱት ጉዳት በህግ እንዲጠየቁ በግልጽ እንደሚያስረዳም አቶ ኡመር ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም አስተዳደሩ መሬት ወስደው ለረጅም ዓመት ሳያለሙ በማስቀመጥ ባደረሱት ጉዳት ግለሰቦቹን በህግ የሚጠይቁበት አግባብ እንደሚኖር ከንቲባው ገልፀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም