ኮቪድ-19 የመንግስት ተቋማት በስብሰባ የሚያጠፉትን ጊዜ በማስቀረት አዎንታዊ ሚና ተጫውቷል

51

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21/2012 ( ኢዜአ) የመንግስት ተቋማት በስብሰባ የሚያጠፉትን ጊዜ በማስቀረት ረገድ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አዎንታዊ ሚና መጫወቱን የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ገለጸ።

ኮሚሽነር በዛብህ ገብረየስ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳሉት በመንግስት ተቋማት ስብሰባ መብዛትና ለተገልጋዩ ፈጣን አገልግሎት ባለመስጠት ተደጋጋሚ ቅሬታ ይቀርብባቸዋል።

ስብሰባዎቹ ጊዜና ገንዘብ ከመፍጀት ባለፈ በውጤት የማይታጀቡ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

ይህ ሲቪል ሰርቪሱን ለተደጋጋሚ ወቀሳ ይዳርግ የነበረው ስብሰባ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መፍትሄ ማግኘቱንም አመልክተዋል።

የኮሮናቫይረስ በዜጎች ላይ እያስከተለ ያለው ጉዳት ከፍተኛ ቢሆንም የመንግስት መስሪያ ቤቶች በስብሰባ የሚያጠፉትን ጊዜ በማስቀረት በኩል ግን 'አዎንታዊ ሚና ተጫውቷል' ነው ያሉት ኮሚሽነር በዛብህ።

"ወረርሽኙ መጥፎ አጋጣሚ ቢሆንም ከዚህ ጠቃሚ ልምዶችና ተሞክሮዎችን በመውሰድ ስብሰባዎቻችንን በራሳችን አገር በለማ ደቦ የኤሌክትሮኒክስ መተግበሪያ መጠቀም እንደሚቻል ኢንሳ ያስታወቀበት ሁኔታ አለ እሱን ተጠቅመን ውይይቶችን እናካሂዳለን፣ መረጃዎችንም እንቀያየራለን" ብለዋል።

ከድህረ ኮቪድ በኋላም በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ አጭር የስራ መረጃዎችን የመለዋወጡ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አክለዋል።

እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ መሰረታዊ የመንግስት ስራዎች ወረርሽኙ በሚፈጥረው አሉታዊ ተጽዕኖ ምክንያት እንዳይቋረጡ የመንግስታቱ ድርጅትም ድጋፍ እያደረገ ነው።

ኮቪድ-19 በኢትዮጵያ ከተከሰተ ጀምሮ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጫና ፈጥሯል።

መንግስት ጫናውን ለመቀነስ ያለውን አቅም በመጠቀም የሚያደርገው ርብርብ በበጎ ፈቃደኞችና በለጋሽ ደርጅቶች እየታገዘም ነው።

የመንግስታቱ ድርጅትም በተለይ መሰረታዊ የመንግስት አገልግሎቶች እንዳይቋረጡ የገንዘብ ድጋፍ ጭምር ማድረጉን ነው ኮሚሽነሩ የገለጹት።

በድርጅቱ ድጋፍ በሚካሄደው ፕሮጀክትም በመጀመሪያ ዙር 20 መሰረታዊ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ተናግረዋል።

ሠላምና ፀጥታ፣ አስተዳደርና ፍትህ፣ ንግድና ገቢ አሰባሰብ ላይ የሚሰሩ ተቋማት ስራቸውን እንዳያቋርጡ በድርጅቱ ድጋፍ ከሚደረግላቸው የመንግስት ተቋማት ዋነኞቹ ናቸው።

በክልሎች ያሉ ተመሳሳይ ተቋማትም በሁለተኛ ዙር ድጋፍ የሚደረግላቸው ይሆናል ብለዋል።

በሌላ በኩል ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ የመንግስት ሠራተኞች በቤታቸው ስራቸውን እንዲከውኑ መመሪያ ቢወጣም አንዳንዶች ተግባራዊ እያደረጉት አለመሆኑን ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል።

ይህም በስራ ቦታ ብሎም በትራንስፖርት አገልግሎት ላይ መጨናነቅ በመፍጠር መመሪያው ውጤታማ እንዳይሆን እያደረገ ነው ብለዋል።

ሠራተኞች ወረርሽኙን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ በመወጣት ራሳቸውን ብሎም ሌሎችን በመጠበቅ አርዓያ እንዲሆኑም ኮሚሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም