የኦፓል ማእድን አምራች ወጣቶች በገበያ ትስስር ችግር ተጠቃሚዎች መሆን አልቻልንም አሉ

491

ደሴ  ሰኔ 21/2012 (ኢዜአ) በደቡብ ወሎ ዞን ደላንታ ወረዳ በኦፓል ማዕድን ቁፈሮ የተሰማሩ ወጣቶች በገበያ ትስስር ቸግርና በህገ ወጥ ደላሎች ጣልቃ ገብነት ምከነያት የልፋታቸውን ያክል ተጠቃሚዎች መሆን እንዳልቻሉ ገለፁ ።

ችግሩን ለመፍታት በ6 ሚሊዮን ብር ወጪ አዲስ የገበያ ማዕከል ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን የወረዳው ቴክኒክ ሙያና ኢንተርፕራይዞች ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

የኦፓል ማእድን በቁፋሮ የሚወጣና ለአንገት ፣ ለጆሮ ፣ ለጣትና ለሌሎች ጌጣጌጦች አገልግሎት የሚውል ነው ተብሏል ።

በደላንታ ወረዳ የ021 ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ተስፋዬ አገዘ ለኢዜአ እንደገለጸው 60 ሆነው በመደራጀት በቀበሌያቸው የኦፓል ማዕድን ቁፋሮ ከጀመሩ ከአምስት ዓመታት በላይ አስቆጥረዋል፡፡

ምርቱ አዋጪ ቢሆንም በገበያ ትስስር እጦትና  ህገ ወጥ ደላሎች  በገበያው  ፈላጭ ቆራጭ በመሆናቸው ምክንያት በሚፈለገው ልክ ተጠቃሚ አለመሆናቸውን ተናግሯል፡፡

"ህይወታችን ለአደጋ አጋልጠን በበረሃ ላይ ቆፍረን በመከራ የምናወጣውን ምርት የምንሸጥበት ቦታ ባለመኖሩ በህገ ወጥ ደላላ አማካኝነት በርካሽ ዋጋ በመሸጥ እስከ አሁን ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ ለመግፋት ተገደናል" ብሏል።

በመሆኑም መንግስት ጠንካራ የገበያ ማዕከል በማቋቋም ትስስር  እንዲ ፈጠርላቸው ጠይቆ ህገ ወጥ ደላሎችንም ከግብይት ሰንሰለቱ እንዲወጡ መደረግ አለበት ብሏል ።

ሌላው የ027 ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ዘሪሁን ሙሉጌታ በበኩሉ "ወጣቶች ተደራጅተን በመከራ የምናገኘውን የኦፓል ምርት ከአምራቹ በላይ ህገ ወጥ ነጋዴዎች እየተጠቀመበት ነው" ሲል ቅሬታውን ገልጿል ።

የገበያ ትስስር ችግሩን ከመፍታት ባለፈ እሴት የሚጨምሩና  ለመቆፈሪያ  የሚያግዙ መሳሪያዎች እንዲቀርብላቸውም ወጣቱ ጠይቋል።

በደላንታ ወረዳ ወገልጤና ከተማ ነዋሪ ወጣት ግዛቸው ሰማኝ እንዳለው ደግሞ የኦፓል ምርት ወደተለያዩ ጌጣጌጦች በመቀየር ህይወቱን እንደሚመራ ተናግሯል፡፡

ይሁን እንጂ ኦፓል ከአምራቾች በተመጣጣሽ ዋጋ እየገዛ ስራውን እንዳያከናውን ህገ ወጥ ደላሎች በመሀል እየገቡ የግብይት ሰንሰለቱ እያመሰቃቀሉት እንደሚገኙ ጠቁሟል ።

ህገ ወጥ ደላሎቹ ዋነኛ የምርቱ ተረካቢ ነጋዴዎች ወደ አካባቢው መጥተው ግዥ እንዳይፈፅሙ ከመከልከል ጀምሮ ግብይቱን በማስተጓጎልና ዋጋን ዝቅ አድርገው እስከ መተመን የሚደርስ ችግር  በመፍጠር  ተጠቃሚ እንዳንሆን አድርጎናል ሲሉ አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል ።

 የደላንታ ወረዳ ቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዮት ጌታሁን እንደገለፁት  በወረዳው ካሉ 33 ቀበሌዎች ውስጥ በ27ቱ የኦፓል ምርት ይገኛል ።

በዘርፉ ወጣቶችን በማደራጀት የስራ እድል ምንጭ ሆኖ እንዲያገለግል ለማድረግ ታቅዶ ወደ ስራው ቢገባም በተለያዩ ችግሮች ምክንያት በሚፈለገው ልክ ውጤታማ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከ6 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ አዲስ የገበያ ማእክል እየተገነባ መሆኑን ጠቁመው በመጪው መስከረም ተጠነቅቆ  አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ገልፀዋል ።

ማዕከሉ ስራ ሲጀምር አምራቾችና ህጋዊ ተረካቢዎችን ቀጥታ በማገናኘት ሁሉም በልፋቱ ልክ ተጠቃሚ ይሆናል ብለዋል ።

የደቡብ ወሎ ዞን ቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዝ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን መኮነን በበኩላቸው ኦፓልና ሌሎች ማዕድናትን ለስራ እድል መፍጠሪያነት ጥቅም ላይ እንዲውሉ እየተደረገ ነው።

በዚህ ዓመት በማዕድን ዘርፍ ለ5 ሺህ 979 ወጣቶች በቋሚነትና በጊዜያዊነት የስራ እድል መፈጠሩንም ገልጸዋል፡፡

በአካባቢው ለብርጭቆና ሲሚንቶ ፋብረካ የሚሆን ግብዓት፣ ኖራ ድንጋ፣ ነዳጅና ሎሎች ማዕድኖችም መኖራቸው በጥናት በመረጋገጡ ትላልቅ ባለሃብቶችን ጭምር እንዲሳተፉ ከፌደራል መንግስት ጋር እየተሰራ ነው ብለዋል ፡፡

በኦፓል ምርት ግብይት እንቅስቃሴ የሚስተዋለውን ክፍተት በተደራጀ አግባብ በቅርቡ ይፈታል፤ አምራኞችም በቴክኖሎጂ እንዲታገዙ ይደረጋል የሚል ምላሽ ሰጥተዋል ።

በደቡብ ወሎ ዞን በዚህ ዓመት በማዕድንና ሌሎች የስራ ዘርፎች ከ127 ሺህ ለሚበልጡ ስራ እጥ ወጣቶች የስራ እድል መፍጠር እንደተቻለ ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመልክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም