በኦሮሚያ ክልል 700 ሚሊየን ችግኖች ተተክለዋል

63

አዲስ አበባ ሰኔ 20/2012 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል በያዝነው ዓመት ለመትከል ከታቀደው 3 ነጥብ 2 ቢሊየን ችግኞች መካከል አስካሁን ከ700 ሚሊዮን በላይ ችግኖች መተከላቸውን የክልሉ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ አስታወቀ። 

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ እንዳልካቸው  ተፈሪ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው  ቆይታ  እንዳሉት ኮቪድ-19ን እየተከላከሉ ተከላው በታቀደለት  የጊዜ  ገደብ  መሠረት እንዲከናወን እየተሰራ ነው።

የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ችግኝ ተከላውን ከግብ ለማድረስ ሁሉም አካላት በተከላ እየተሳተፉ መሆናቸውን  አመልክተዋል።

ችግኞች መትከልና መንከባከብ የአንድ ሴክተር መሥሪያ ቤት ሥራ ብቻ ሳይሆን፤ ዜጎች የሚሳተፉበት ተግባር መሆን እንዳለበትም ጠቁመዋል።

ችግኝ መትከል የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ መሆኑንም አቶ እንዳልካቸው አስረድተዋል።

በክልሉ ዘንድሮ ዓመት የችግኝ ተከላው ሰፋ ባለ መልኩ መታቀዱን የገለጹት ምክትል ኃላፊው፣ አፈጻጸሙም እስካሁን በተያዘለት የጊዜ ገደብ  እየተከናወነ ይገኛልም ብለዋል።

አሁን ላይ የኮቪድ-19 በሽታ ተጽእኖ ቢኖርም፤ የችግኝ ተከላውን እንዳላስተጓጎለው አስረድተዋል።

በክልሉ የችግኝ ተከላ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶም እስካሁን ድረስ ከ700 ሚሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውን ተናግረዋል።

በተከላው አምስት ሚሊየን የሚሆኑ ሕዝብ በ245 ሺህ የልማት ቡድኖች  ተደራጅቶ  መሳተፉን ገልጸዋል።

የተከላ መርሐ ግብር እስከሚጠናቀቅበት ሐምሌ 20/2012 ድረስም በዕቅድ የተያዘው 3 ነጥብ 2 ቢሊየን ችግኞች እንደሚተከሉም ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ በተያዘው የክረምት ወቅት አምስት ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል በአገር አቀፍ በመካሄድ ላይ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም