ኤርትራ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አካል ሆና ገንቢ ሚና እንድትጫወት ኢትዮጵያ ጠንክራ ትሰራለች -ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ

88
አዲስ አበባ ሀምሌ 2/2010 ኤርትራ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አካል ሆና ገንቢ ሚና እንድትጫወት ኢትዮጵያ ከተለያዩ አካላት ጋር በትብብር እንደምትሰራ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ገለጹ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በጽህፈት ቤታቸው በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የኤርትራ ጉብኝትና በደቡብ ሱዳን ወቅታዊ የሰላም ጉዳይ ላይ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። ዶክተር ወርቅነህ ኤርትራ አሁን ካለችበት ሁኔታ ወጥታ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አካል ሆና ገንቢ ሚና እንድትጫወት ኢትዮጵያ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እንደምትሰራ ነው የገለጹት። በኤርትራ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተጣሉበት ማዕቀብ እንዲነሳላት የሚደረገውን ጥረት ኢትዮጵያ ከሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የምትሰራው ይሆናል ነው ያሉት ሚኒስትሩ። ኤርትራ ወደ ምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) በመግባት በቀጠናው የሰላም ሃይል ሆና በጋራ የምትሰራበትና ከሌሎች እህት አገራት ጋርም በቅንጅት የምትሰራበት ሁኔታ ማመቻቸትም የሁለቱ አገራት ስምምነት አካል ነው ብለዋል። ኢትዮጵያና ኤርትራ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ከማሻሻል ባለፈ በአፍሪካና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ተቀናጅተው በመስራት በጎ አስተዋጽኦ ለማበርከት ከስምምነት ላይ መደረሱንም ተናግረዋል። የሁለቱ አገራት መሪዎቹ በስምምነታቸው የአገራቱን ብሎም የህዝቦችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰሩም መግለጻቸውን አስታውሰዋል። ከምንም በላይ የሁለቱ አገራት ህዝቦችን ማቀራረብና ለ20 ዓመታት በነበረው አለመግባባት አገራቱ ማግኘት የሚገባቸውን ጥቅም አለማግኘታቸው ያስከተለውን ጉዳትና ያጣነውን ነገር መልሶ በማግኘት ላይ መስራት የአገራቱ መሪዎች ዋነኛ የውይይት አጀንዳ እንደነበርም ገልጸዋል። አገራቱ የፈረሟቸውን የወዳጅነት ስምምነቶች ተፈጻሚነት የሚከታተል ኮሚቴ መቋቋሙንና ስራውን ዛሬ መጀመሩንም ነው ዶክተር ወርቅነህ ያስታወቁት። በኤርትራ የሚገኙ እስረኞችና ምርኮኞች ጉዳይ፣ የድንበር ጉዳዮች፣ የወደብ አጠቃቀም፣ የአልጀርስ ስምምነት አተገባበርና ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊና ጉዳዮችን ኮሚቴው እንደሚከታተል አመልክተዋል። ኮሚቴው በትራስንስፖርት ረገድም የአየርና የየብስ ትራንስፖርት ታሪፍና ሌሎች ጉዳዮች በዝርዝር እንደሚያይም ተናግረዋል። በቀጣዩ ሳምንት በሁለቱ አገራት መካከል በሚጀመረው በረራ የሁለቱ አገራት ዜጎች አገራቱ ሉዓላዊ ከመሆናቸው አንጻር አንዱ ወደ አንዱ አገር ሲገባ ቪዛ እንደሚጠየቅና በቀጣይ መንገደኞች ያለ ቪዛ የሚገቡበት ጉዳይ ላይም ኮሚቴው እንደሚሰራ አስታውቀዋል። ኮሚቴው በተደረሱ ስምምነቶች ላይ የሚነሱ ሀሳቦችን በጥልቀት በመመልከት ወደ ትግበራ በሚገቡበት ሁኔታና ስምምነቶቹን ተፋጻሚ ለማድረግ የሚያስችል የጊዜ ሰሌዳ እንደሚያወጣም ነው ዶክተር ወርቅነህ ያስረዱት። አገራቱ የደረሱት ስምምነት በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ያለውን የፖለቲካ ስነ ምህዳር የቀየረና በጣም ከፍተኛ በሚባል ሁኔታ ተጽእኖ የፈጠረ መሆኑንም አስረድተዋል። አገራቱ ማንንም ጣልቃ ሳያስገቡና ሶስተኛ ወገን ሳይኖር ስምምቱን መፈራረማቸው ስምምነቱን ልዩ እንደሚያደርገውም አስታውቀዋል። የደረሰው ስምምንትና ጉብኝት የአገራቱን ግንኙነት ለማሻሻል የተወሰደ የመጀመሪያ እርምጃ ብሎ መውሰድ እንደሚቻልና በቀጣይም አገራቱ ዘላቂነት ባለው መልኩ ያላቸውን ትስስር ለማጠናከር ብዙ እንደሚሰሩ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ በኢትዮ-ኤርትራ ጉዳይ ላይና በሌሎች የሰላም ጉዳዮች ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እየሰሩት ላለው ስራ የሰላም ሽልማት ይገባቸዋል ብላ እንደምታምንም ገልጸዋል። ከደቡብ ሱዳን ጋር በተያያዘም የኢጋድ ሊቀመንበር የሆነችው ኢትዮጵያ የአገሪቷ ተቀናቃኝ ሃይሎች አሁን ላይ ለደረሱት ስምምነት ወሳኝ ሚና መጫወቷንም ተናግረዋል። የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርና የተቀዋሚ ሃይል መሪ ዶክተር ሪክ ማቻር በአዲስ አበባና ካርቱም ውይይት ማድረጋቸውን አስታውሰው በያዝነው ሳምንት በኡጋንዳ በቀጣይ ሳምንት ደግሞ በኬንያ ሁለቱ መሪዎች ቀጣይ ውይይት እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም