የኤሌክትሪክ ኃይል አስተላላፊ የሆነ ትራንስፎርመር በክሬን ጭነው ለማምለጥ የሞከሩ ተያዙ

93

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20/23012(ኢዜአ) የመብራት ኃይል ሠራተኞች ነን በሚል በቦሌ ክፍለ ከተማ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል አስተላላፊ የሆነ ትራንስፎርመር በክሬን ጭነው ለማምለጥ ሲሞክሩ እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን ፖሊስ አስታወቀ።

በአካባቢው ነዋሪዎች ጥርጣሬ ለፖሊስ በተሰጠ ጥቆማ እሰከጫኑበት ክሬን እጅ ከፍንጅ ሊያዙ መቻላቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቋል፡፡

ከመሥሪያ ቤቱ ዕውቅና ውጭ የመብራት ኃይል ሠራተኞች ነን በሚል ማጭበርበሪያ በኤሌክትሪክ ኃይል ላይ ወንጀሎችን የሚፈጽሙ ግለሰቦች እየተበራከቱ በመሆኑ ኅብረተሰቡ ለኤሌክትሪክ ኃይል ንብረቶች ተገቢውን ጥበቃ እንዲያደርግ ፖሊስ ጠቁሟል፡፡

በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ሐያት ቁ.1 አካባቢ ትናንት ከቀኑ 9፤30 አካባቢ የሚገኘውን ትራንስፎርመር ከመስሪያ ቤቱ ዕውቅና ውጭ ኮድ 3 ኢት84535 በሆነ ክሬን ተሸከርካሪ ታግዘው ሰርቀው ለማምለጥ ሲሞክሩ መያዛቸውን በቦሌ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ የወንጀል መከላከልና የማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት ም/ዳይሬክቶሬት የሆኑት ኮማንደር ያሲን ሁሴን ለአዲስ ፖሊስ ገልጸዋል፡፡

ፖሊስ የምርመራ ሂደቱን ለመቀጠል ተጠርጣሪዎቹንና በእግዚቢትነት የተያዙ ንብረቶችን በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ መጀመሩን ኮማንደር ያሲን ሁሴን ገልጸዋል።

የመብራት ኃይል ሠራተኞች ነን በሚል የሚመጡ ግለሰቦች ሲያጋጥሙት ሕጋዊ ሠራተኞች ስለመሆናች በአግባቡ ማረጋገጥ ይኖርበታል ሲሉ ኃላፊው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በተመሣሣይ ዜና ቦሌ ክፍለ ከተማ ለሚ የኢንዱስትሪ ፓርክ አካባቢ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል አስተላላፊ ማማ የቆመበት ቅስት ብረቶች ባልታወቁ ሰዎች በመሰረቃቸው መውደቁን ማረጋገጡን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል።

ከትናንት በስቲያ ለሚ የኢንዱስትሪ ዞን አካባቢ የመብራት ኃይል መቋረጡን መረጃ የደረሰው ፖሊስ በአካባቢው በመድረስ መውደቁን አረጋግጦ ጥበቃ እያደረገለት እንደሚገኝ የቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ አስታውቋል፡፡

ወንጀል ፈጻሚዎቹን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ፖሊስ ብርቱ ክትትል እያደረገ መሆኑን ኮማንደር ያሲን ማስታወቃቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዘገባ አመልክቷል።

ኮማንደሩ የወንጀል ድትጊቱ ኢኮኖሚያዊ ጫናው ከፍተኛ ስለሆነ ነዋሪዎች አካባቢያቸውን እንዲጠብቁና ከፀጥታ አካላት ጋር ያላቸውን ትብብር አጠናክረው እንዲቀጥሉ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ዘገባው አመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም