የሕዳሴ ግድብን የውኃ ሙሌት ጊዜ እንደተራዘመ የውጭ መገናኛ ብዙኃን እየዘገቡ ያለው ውሸት ነው-- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

60

ሰኔ፣20/2012 (ኢዜአ) የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌትን በተመለከተ አል አህራም፣ አልጀዚራና ሮይተርስ እያሠራጩ ያለው ዘገባ ትክክል አለመሆኑን አስታወቀ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ከአብመድ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደተናገሩት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የውኃ ሙሌት በተያዘለት ጊዜ ይከናወናል፡፡

‘‘የኢትዮጵያ መንግሥት አቋም ግልጽ ነው፤ ዓለማቀፍ ሕግጋትንም እናከብራለን’’ ያሉት አምባሳደር ዲና ግድቡን ለመገንባት የማንም ፈቃድ እንዳልተጠየቀው ሁሉ ለውኃ ሙሌቱም ፈቃድ እንደማያስፈልግና በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል፡፡

ዛሬ አል አህራም፣ ሮይተርስ እና አልጀዚራ የተሰኙ የመገናኛ ብዙኃን የውኃ ሙሌቱ ሦስቱ ሀገራት ስምምነት እስኪደርሱ እንደተራዘመ አስመስለው የዘገቡት ዘገባ የተሳሳተና የጋራ አቋም ያልተያዘበት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ግብጽ ‘‘የአፍሪካን ችግር በአፍሪካ መፍታት’’ የሚለውን መርህ ተቀብላ በድጋሜ ወደ ድርድሩ መመለሷ መልካም መሆኑን የጠቀሱት አምባሳደር ዲና በድርደሩ ይነሱ የነበሩ የቴክኒክና የሕግ ጉዳዮችን በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት በቀጣይ ሁለት ሳምንታት ተነጋግሮ መልክ ለማስያዝ መግባባት ላይ መደረሱን አስታውቀዋል፡፡

‘‘የውኃ ሙሌቱን ግን በተያዘለት መርሀ ግብር መሠረት ይቀጥላል’’ ነው ያሉት፡፡

ከአብመድ ጋር በስልክ ቆይታ ያደረጉት የውኃ መስኖና ኢነርጅ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለም (ዶክተር ኢንጂነር) የአፍሪካን ችግር በአፍሪካ ለመፍታት ከኅብረቱ ጋር በመሆን ውይይት መጀመሩ መልካም መሆኑን በመጥቀስ በቀጣይ ሁለት ሳምንታት እልባት ለመስጠት አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸዋል፡፡

ግብጽ ጉዳዩን ወደተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት መውሰዷን ተከትሎ ምክር ቤቱ ሰኞ እንደሚወያይበት መርሀ ግብር መያዙን በተመለከተ ለተነሳላቸው ጥያቄም ‘‘የፀጥታው ምክር ቤት ጉዳዩ ወደ አፍሪካ ኅብረት መመለሱን እንዲያውቀው መደረጉን ተከትሎ ምን እንደሚወስን ወደፊት የምናዬው ይሆናል’’ ብለዋል፡፡

ቀጣይ ውይይቶች በፖለቲካ መሪዎች ሳይሆን በቴክኒክ ባለሙያዎች እንደሚቀጥሉ መግባባት ላይ መደረሱንም አስታውቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ ጥያቄ መሠረት የሦስትዮሽ ውይይቱን ደቡብ አፍሪካ እንድትታዘብ መመረቷንና የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤና የአውሮፓ ኅብረትም እንደሚታዘቡት ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡

ውሳኔው የሦስቱ ሀገራት የጋራ ስምምነት ብቻ እንደሚሆንም ተናግረዋል፡፡

የግድቡን የውኃ ሙሌት በተመለከተ ግን በኢትዮጵያ በኩል ተለዋጭ ሐሳብ እንደሌለና በተያዘው መርሀ ግብር መሠረት እንደሚቀጥል ነው ዶክተር ኢንጂነር ስለሽ ያስታወቁት፡፡

‘‘የውኃ ሙሌቱ ማንም የሚያስቆመው አይደለም’’ ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም