የዋቢ ሸበሌ ወንዝ የሚያስከትለውን ጉዳት መቀነስ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት ተካሄደ

119
ጅግጅጋ ግንቦት 1/2010 የዋቢ ሸበሌ ወንዝ ሲሞላ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት መቀነስ በሚቻልበት መንገድ ከነዋሪዎች ጋር ውይይት መደረጉን የሶማሌ ክልል አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ቢሮ አስታወቀ፡፡ ሰሞኑን የዋቢ ሸበሌ ወንዝ ሞልቶ ባስከተለው ጉዳት በክልሉ ለተፈናቀሉ 16 ሺህ 336 ቤተሰቦች የቤት ቁሳቁስና የእህል እርዳታ መከፋፈሉን ቢሮው ገልጿል፡፡ የቢሮው የቅድመ ማስጠንቀቂያ ኪዝ ቲም አስተባባሪ አቶ ዩሱፍ ኡስማን ለኢዜአ እንዳሉት በላይኛው ተፋስስ አካባቢዎች ዝናብ ሲጥል በታችኛው ተፋሰስ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ላይ ጉዳት ያደርሳል፡፡ ችግሩን ለመከላከል የክልሉ መንግስት በዋቢ ሸበሌ ወንዝ ዳር የሚገኙ ነዋሪዎችን ከወንዙ አርቆ ለማስፈር ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ይህንኑ አስመልክቶ የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሃመድ ኡመር ከሙስታሂል ከተማ ነዋሪዎች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ ውይይቱ በዋቢ ሸበሌ ወንዝ ዳር የሚገኙ ነዋሪዎች ከወንዙ ሶስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ መስፈር በሚችሉበት አግባብ ላይ ያተኮረ እንደነበርም አስታውቀዋል፡፡ ከውይይቱ ጎን ለጎን በቅርቡ ወንዙ ሞልቶ ባስከተለው ጉዳት ለተፈናቀሉ ቤተሰቦች ከ10 ሺህ 448 ኩንታል በላይ የበቆሎ፣ ሩዝ፣ ዘይትና መሰል የእለት ደራሽ እርዳታ ተከፋፍሏል፡፡ በተጨማሪም ከ20 ሺህ በላይ ድንኳን፣ ብርድ ልብስና የተለያየ የቤት መገልገያ ቁሳቁስ መከፋፈሉን ገልፀዋል፡፡ በቀላፎ ወረዳ አለው ኢጋድሲ ቀበሌ ነዋሪዋ ወይዘሮ ከልቱን አብዲ እርዳታው ቢዘገይም በጎ ጅምር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሌላው የደበከቶር ቀበሌ ነዋሪ አቶ አብዲ አህመድ ስለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነው በቀጣይ መልሰው እንዲቋቋሙ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም