የሳውላ ሆስፒታል ማስፋፊያ ግንባታ መዘግየት ለህብረተሰቡ ፈጣን አገልግሎት መስጠት አላስቻለም

52
አርባምንጭ ሀምሌ 2/2010 የሳውላ ሆስፒታል የማስፋፊያ ህንጻዎች ግንባታ መዘግየት ለህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት እንዳይሰጥ እያደረገው መሆኑን የሳውላ አጠቃላይ ሆስፒታል አስታወቀ፡፡ ስንታየሁ ኤብሶ አጠቃላይ የህንፃ ተቋራጭ በበኩሉ የግንባታ ዕቃዎች ዋጋ ጭማሪ ሥራውን እንዳይጀምር ማድረጉን ገልፀዋል፡፡ በ2008 ዓ.ም ከመጀመሪያ ደረጃ ወደ አጠቃላይ ሆስፒታል ያደገው የሳውላ አጠቃላይ ሆስፒታል ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጥ ስድስት የማስፋፊያ ህንፃዎችን ማስገንባት እንደሚኖርበት የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ማርቆስ ማኖቴ ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡ የሚገነቡ ህንፃዎችም የመድሃኒት ክፍል፣ የማዋለጃ፣ የክትባት ፣የስኳርና የልብ ህክምና አገልግሎቶች የሚሰጥባቸው መሆናቸውን  ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡ የግንባታ ጨረታውን ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ  በሆነ ዋጋ ያሸነፈው ስንታየሁ ኤብሶ የህንፃ ተቋራጭ ስድስት ሚሊዮን ብር ቅድመ ክፍያ ወስዶ ግንባታውን ሳይጀምር ከአንድ ዓመት በላይ ቆይቷል፡፡ የማስፋፊያ ግንባታው በ2009 ዓ.ም መጨረሻ ተጀምሮ በ2010 የበጀት ዓመት መጨረሻ ላይ ርክክብ መፈጸም ቢኖርበትም ግንባታው እስከ ዛሬ ባለመጀመሩ የመልካም አስተዳደር ጥያቄ እያስነሳ ይገኛል ፡፡ ሆስፒታሉ በዙሪያው በሚገኙ ዘጠኝ ወረዳዎችና በአንድ የከተማ አስተዳደር ለሚገኙ ከ1 ሚሊዮን በላይ ለሚሆን ህዝብ አገልግሎት እንደሚሰጥ የጠቆሙት የሳውላ አጠቃላይ ሆስፒታል መዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ምንያህል አሰፋ ናቸው፡፡ የማስፋፊያ ግንባታው በመጓተቱ ምክንያት የህክምና መሣሪያዎች አቅርቦት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ መፍጠሩን ተናግረዋል ፡፡ በተጨማሪም የውስጥ ደዌ፣ የልብ፣ የኩላሊት፣ የጉበትና የስኳር እንዲሁም  የጽንስና ማህፀን ህክምና መሣሪያዎችንም ሆነ የዘርፉ ባለሙያዎችን ለማሟላት ሆስፒታሉ መቸገሩን ጠቅሰዋል ፡፡ በሳውላ ከተማ የኩስቲ ቀበሌ ነዋሪ አቶ በቀለ ዑታ በሳውላ ሆስፒታል የልብ ህክምና አገልግሎት ባለመኖሩ የሁለት ዓመት ልጃቸውን አዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እየተመላለሱ ለማሳከም መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡ በዚሁም ከ15 ሺህ ብር በላይ የህክምናና ለሌሎች ወጪዎች እንዳወጡ ገልጸዋል ፡፡ የማስፋፊያ ህንጻ ግንባታውን ለማከናወን ጨረታውን ያሸነፈው ተቋራጭ ባለቤት አቶ ስንታየሁ ኤብሶ በበኩላቸው የዶላር ዋጋ ማስተካከያውን ተከትሎ በግንባታ ዕቃዎች ላይ በተከሰተው የዋጋ ጭማሪ የግንባታ ዕቃዎችን ለመግዛት በመቸገራቸው መዘግየቱን  አስረድተዋል ፡፡ መፍትሄ እስኪገኝ ድረስ ግንባታውን መጀመሩ አስፈላጊ በመሆኑ በግንባታው ስፍራ የንብረት ክፍል መገንባቱን ጠቅሰው የባለሙያ ምደባ የተደረገ በመሆኑ  ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ ግንባታው እንደሚጀመር ጠቁመዋል ፡፡          
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም