የሚተከሉ ችግኞችን ተንከባክቦ ማሳደግ ባህል ሊሆን ይገባል….ወይዘሮ ፊልሰን አብዱላሂ

64

ባህርዳር፣ ሰኔ 20/2012 (ኢዜአ) የአካባቢ የአየር ንብረት ተፅኖ ለመቀነስና የህዳሴ ግድብን በደለል ከመሞላት ለመከላከል የሚተከሉ ችግኞችን ተንከባክቦ ማሳደግ ባህል ሊሆን ይገባል ሲሉ የኢፌዴሪ ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትር ገለጹ።

የአማራ ክልል የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳታፊ የወጣት አደረጃጀቶች በባህርዳር ዙሪያ ወረዳ ሰባታሚት ተብሎ በሚጠራው ቀበሌ የችግኝ ተከላ ዛሬ ተከናውኗል።

ሚኒስትሯ ወይዘሮ ፊልሰን አብዱላሂ በክረምት የበጎ ፈቃድ የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር ላይ ተገኝተው እንደገለጹት ችግኝን መትከል ብቻ ሳይሆን ተንከባክቦ ማሳደግ ባህል ሊሆን ይገባል።

"የነገ ሀገር ተረካቢ የሆነው የወጣት አደረጃጀትም በክረምት ወቅት በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በየተፋሰሱ የሚተክላቸውን ችግኞች ተንከባክቦ ሲያሳድግ የጣና ኃይቅንም ሆነ የህዳሴውን ግድብ በደለል ከመሞላት ስጋት ይታደጋል"ብለዋል።

ይህም የሃገሪቱ ህዝቦችና የተፋሰሱ ሀገራት የጋራ ሃብቶቻቸውን ከስጋት በመታደግ በሚሰጡት አስተዋጽኦ ልክ በዘላቂነት እንዲጠቀሙ እንደሚያስችላቸውም አስረድተዋል።

በዚህ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የአዲስ አበባ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪ ወጣቶች ተገኝተው አሻራቸውን በማስቀመጣቸውም አመስግነዋል።

"የጋራ ሃብታችን በሆነው የጣና ኃይቅ ላይ የተደቀነውን የእምቦጭ አደጋ በጋራ ተረባርበን ልናስወግደው ይገባል" ሱሉም ሚኒስትሯ አሳስበዋል።

የክልሉ ሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አባይነህ መላኩ በበኩላቸው በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ከ4 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች በተለያዩ የልማት ስራዎች ይሳተፋሉ።

"ለአረንጓዴ አሻራ እውን መሆን ዛሬ የተተከሉትን አንድ ሺህ 150 ችግኞችን ጨምሮ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ማንጎ፣ አቮካዶ፣ ግራቪሊያና ሌሎች ችግኞችን ወጣቱ በያለበት አካባቢ ተንከባክቦ ያሳድጋል" ብለዋል።

"በጎነት ለአብሮነት" በሚል ጣናን ለመታደግ ከአዲስ አበባ እንደመጡ የገለጹት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወጣቶችና በጎ ፈቃድ አገልግሎት ማስተባበሪያ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብርሃም ታደሰ ናቸው።

"ጣና ብሄራዊ ጉዳያችን ከመሆኑም በላይ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ መሰረት በመሆኑ አጋርነታችንን ለማሳየትና እምቦጭን ለመከላከል ከ100 በላይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች መጥተዋል"ብለዋል።

በችግኝ ተከላው መሳተፋቸው ልባዊ ኩራት እንደተሰማቸው ገልጸው፤ "ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብቷ የዳበረና ለትውልድ ሊተላለፍ በሚችል መልኩ ሁሉም ሊሰራ ይገባል" ብለዋል።

የአማራ ክልል ወጣቶች ማህበር ሊቀመንበር ወጣት አባይነህ ጌጡ በበኩሉ እንደገለጸው በያዝነው የክረምት ወቅት በሁሉም አደረጃጀቶች 4 ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ችግኞች የመትከል ስራ ተጀምሯል።

"በችግኝ ተከላውም አንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን የሚሆኑ ወጣቶች እንደሚሳተፉ ገልጾ የተተከሉ ችግኞችንም ተንከባክበው ለውጤት እንዲያበቁ የመደገፍ ስራ ይከናወናል"ብሏል።

በክልሉ በዘንድሮው የክረምት ወቅት ከአንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን በላይ ችግኝ የሚተከል ሲሆን በዛሬው የችግኝ ተከላ መርሀ-ግብርም የፌዴራልና የክልል እንዲሁም የወጣት አደረጃጀት አመራሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም