ኢትዮጵያ በመጪዎቹ ሁለት ሳምንታት የግድቡን ቀሪ የግንባታ ስራዎች በማጠናቀቅ ሙሌት ትጀምራለች

63

አዲስ አበባ ሰኔ 20/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በመጪዎቹ ሁለት ሳምንታት የግድቡን ቀሪ የግንባታ ስራዎች በማጠናቀቅ ሙሌት እንደምትጀምር የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በሁለቱ ሳምንታትም ጊዜ ውስጥ ሶስቱ አገራቱ በግድቡ ዙሪያ ከስምምነት ለመድረስ ወስነዋል።

በትናንትናው እለት በተካሄደው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ቢሮ ስብሰባ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሙሌት እና ውሃ አለቃቀቅ ደንብ ላይ በኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ መካከል እየተካሄደ ባለው ድርድር ላይ ምክክር ተካሂዷል፡፡

ስብሰባው የተጠራው የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ፕሬዝዳንት በሆኑት የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛ ሲሆን የኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ እንዲሁም የጉባኤው አባል የሆኑት ኬኒያ፣ ማሊ፣ የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ መሪዎች ተሳትፈዋል፡፡ 

መሪዎቹ የአባይና የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይ የአፍሪካ ጉዳይ በመሆኑ ከአፍሪካ የሚመነጭ መፍትሄ እንደሚያስፈልገው አስምረበውበታል፡፡

በዚህ ረገድ ድርድሩ ስላለበት ሂደት ከኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን መግለጫዎች የቀረቡ ሲሆን በቀጣይ ስለሚኖረው ሂደት አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

በዚህ መሰረት በግድቡ ሙሌት እና አስተዳደር ላይ የሚደረገው ድርድር በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት እንዲጠናቀቅ መስማማታቸውን የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ለኢዜአ አስታውቋል፡፡

ኢትዮጵያ በመጪዎቹ ሁለት ሳምንታት የግድቡን ቀሪ የግንባታ ስራዎች በማጠናቀቅ ሙሌት ትጀምራለች፤ በነዚህ ሁለት ሳምንታትም ሀገራቱ ከስምምነት ለመድረስ ወስነዋል ነው ያለው። 

በተጨማሪም የአፍሪካ ህብረት ጉዳዩን መመልከት መጀመሩ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤት እንዲገለጥ፣ የአፍሪካ ህብረት እና የመሪዎች ጉባኤ ቢሮ አባላት ድርድሩን እንዲደግፉ፣ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ ከቃላት መካረር እና አላስፈላጊ መግለጫዎች እንዲቆጠቡ አቅጣጫ ተቀምጦ ልዩ የመሪዎች ስብሰባው ተጠናቋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም