በመዲናዋ በ 5 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ወጪ የከተማ አውቶቡስ ፍጥነት መንገድ ግንባታ ተጀመረ

74

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20/2012 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ከተማ በ 5 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ወጪ የከተማ አውቶቡስ ፍጥነት መንገድ ግንባታ ተጀመረ። ወጪው ከፈረንሣይ መንግሥት ብድርና በከተማ አስተዳደሩ ይሸፈናል።

በአዲስ አበባ ከጀሞ ቁጥር 2 እስከ ጄኔራል ዊንጌት አደባባይ የሚዘለቀውን የመንገድ ግንባታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድና የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ታከለ ዑማ በጋራ አስጀምረውታል።

በሁለት ዓመታት ግንባታው የሚጠናቀቀው መንገድ 19 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር ይሸፍናል።

የመንገዱ ግንባታ ወጪው 55 በመቶ በከተማ አስተዳደር፤ ቀሪው 45 በመቶ ደግሞ ከፈረንሳይ መንግሥት በተገኘ ብድር  ይሸፈናል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ ለዘመናዊ ከተማ አስፈላጊ ከሆኑ መሠረተ ልማት ተቋማት መካከል መኖሪያ ቤት፣ የብዙሃን ትራንስፖርትና መንገድ ዋነኞቹ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

አስተዳደሩ ለመሠረተ ልማት ተቋማት ግንባታን ቀዳሚ ተልዕኮው አድርጎ መንቀሳቀስ እንዳለበትም አሳስበዋል።

የመንገዱ ግንባታ በከተማዋ የሚታየውን ሥራ አጥነት በእጅጉ እንደሚቀንሰውና በቂ ዕውቀትና ልምድ እንደሚገኝበትም አስታውቀዋል።

ግንባታን መጀመር ብቻ ሳይሆን በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ቀን ከሌሊት ሰርቶ ማጠናቀቅ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሳስበዋል።

በአዲስ አበባ የቀላል ባቡር ግንባታ ወቅት የታየው ግራና ቀኙን የመነጠል ስህተት በግንባታው ላይ መደገም የለበትም ብለዋል።

በከተማዋ በመንግሥትና በግል ባለሀብቱ ጥምረት በቂ የመኖሪያ ቤቶችን በመገንባት ኅብረተሰቡ የኪራይ ቤቶች የሚያገኝበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በተጨማሪ በአካባቢ ጽዳትና ጥበቃ ላይ ትኩረት አድርጎ እንዲሰራ አሳስበዋል።

ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ዑማ በበኩላቸው የፈጣን አውቶበስ መንገድ ግንባታው በከተማዋ ከተጀመረው የብዙሃን ትራንስፖርት ማስፋፊያ አንዱ ነው ብለዋል።

አስተዳደሩ ግንባታው በተቀመጠለት ጥራትና ጊዜ ለማጠናቀቅ ጠንከሮ ይሰራል ብለዋል።

በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ ከተሞችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተጨማሪ ፕሮጀክቶች እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።

በቀጣይ ወደ ጎሮና ቡራዩ የሚያደርሱ ተመሳሳይ ግንባታዎች እንደሚከናወኑ ምክትል ከንቲባው አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም