ኢትዮጵያና ኤርትራ የጀመሩት የሰላም እንቅስቃሴ ተለያይቶ ለኖረው ህዝብ አዲስ ምዕራፍ ነው

90
አዲስ አበባ ሀምሌ 2/2010 በሁለቱ አገሮች የጠፋው ሰላም የአገሮቹን ኢኮኖሚና የእርስ በእርስ ግንኙነት ከመጉዳት ባለፈ ዜጎች የእናት፣ የአባታቸውን  ሀዘን እንዳይካፈሉ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን በአዲስ አበባ የሚኖሩ ኤርትራዊያን ተናገሩ፡፡ ኤርትራዊው ወጣት ሙሉጌታ ሙሀባው የሚኖረው በኢትዮጵያ አዲስ አበባ ነው። ከሚወዳቸው እናቱና መላው ቤተሰቡ ጋር ያለው ግንኙነት ከተቋረጠ ሁለት አስርት ዓመታት ነጉደዋል። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ተፈጥሮ የነበረው ግጭት ነው። ይህ ግጭት ታዲያ በመንፈስ እንጂ በአካል ከተለያቸው ዓመታት ያለፉትን እናቱን ጨምሮ በወሬ ብቻ የሚያውቀውን ታናሽ ወንድሙንና መላው ቤተሰቦቹን እንደናፈቀ እንዲኖር አስገድዶት ነበር። ''ዛሬ ግን ህልም እንጂ እውን በማይመስል ክስተት ዓመታት የተሻገረው ይህ የናፍቆት ንዳድ ወደአስደሳች ምእራፍ የተሸጋገረ ይመስላል'' ሲል ወጣቱ ተስፋ ማድረጉን ይናገራል። ''ፍቅር አሸነፈ፤ ለ20 ዓመት የናፈቅኳትና ምስሏ ከአእምሮዬ እየደበዘዘ የመጣችውን እናቴን ላያት ነው፤ ከቤተሰቤ ጋር ስለያይ እናቴ ማህጸን ውስጥ ተፀንሶ የነበረው ታናሽ ወንድሜን ላየው መሆኔን ሳስብ ደስታዬ ወሰን አጣ፤ በደስታም እምባዬ በጉንጮቼ ወረዱ፤" ይህን ዓይነቱን አስከፊ ሁኔታ ሌሎች አያሌዎችም ይጋሩታል። ሆኖም አሁን የተጀመረው የሰላም ጥረት ሁኔታዎችን እንደሚለውጥም በማመን ተስፋቸው ለምልሟል። በአዲስ አበባ የሚኖሩት ኤርትራውያን እንደሚሉት በሁለቱ አገሮች መካከል ለዓመታት የቆየውን የጥርጣሬና የጠላትነት ግንኙነት በማስወገድ ለጋራ ጥቅም በትብብር ለመስራት የተጀመረው ጥረት በተለይ ተለያይተው የኖሩትን ህዝቦች ለማገናኘት የሚያስችል አዲስ ምእራፍ ነው። የተፈጠረው መልካም ነገር በጋብቻ፣ በባህል፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካና በኢኮኖሚ ለዘመናት ተሳስረው የኖሩትን ህዝቦች ከማቀራረብ ባሻገር ወላጅና ልጆችን ጨምሮ በግጭቱ ሳቢያ ተለያይተው ለቆዩ ቤተሰቦችና ማህበረሰቦች ታላቅ ብስራት ነው ብለዋል። ወጣት ሙሉጌታ ኢትዮጵያ ሰው ተሳስቦና ተፈቃቅሮ የሚኖርባት አገር ብትሆንም የቤተሰብ በተለይም የእናት ናፍቆት ግን እንቅልፍ ይነሳል  ይላል። የ80 ዓመት አዛውንት የሆኑት ኤርትራዊው የህግ ባለሙያ አቶ ስዩም ወልደገብርኤል እንደሚሉት ደግሞ አዲስ እያዩት ያለው የሰላምና የፍቅር ግንኙነት ለዘመናት ሲናፍቁት የነበረችው ጸሃይ አንድ ቀን እንደምትወጣ ዘውትር ሲያልሙት የነበረው ተስፋቸው እንደሰመረ በእምባ ታጅበው ይናገራሉ። በአሁኑ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከመጡ በኋላ ብዙ ተስፋ ማየታቸውንና በመልክ፣ በባህል፣ በሃይማኖት፣ በአለባበስ፣ በአኗኗርም አንድ የሆነውን ህዝብ በማገናኘታቸው ምስጋናቸው ከፍ ያለ መሆኑንም ተናግረዋል። የሁለቱ አገሮች ህዝቦች በደም የተሰሰሩ በመሆናቸው አንድ ቀን ሰላም መጥቶ ወደ ቀደመ ፍቅራቸው እንደሚመለሱ ተስፋ እንደነበራቸው የሚናገሩት ደግሞ ወይዘሮ አበባ ወልደገብርኤል ናቸው። በሁለቱ አገሮች የጠፋው ሰላም የአገሮቹን ኢኮኖሚና የእርስ በእርስ ግንኙነት ከመጉዳት ባለፈ ዜጎች የእናት፣ የአባታቸውንና ዘመዶቻቸው ሀዘን እንዳይካፈሉ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን ተናግረዋል። ወይዘሮ አበባ'' የ20 ዓመት የጸብ ግድግዳ ፈረሰ በባዶ ሜዳ እንደ ቁራ ጮኬ በሃሳቤ የቀበርኳቸውን እናትና አባቴን አስከሬን ያረፈበትን ቦታ አይቼ እርሜን የማወጣበት ጊዜ ደረሰ፤ ፈጣሪ ይመስገን በአንድ ብላቴና የጸቡ ግድግዳ ፈርሷል" ሲሉ ጥረቱን አድንቀዋል። እርሳቸውም የእናትና የአባታቸውን ሃዘን እስካሁን ከሆዳቸው እንደልወጣ ይናገራሉ። የተጀመረው የፍቅር ድልድይ ቀጣይነት እንዲኖረው ሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች በጋራ እንደሚሰሩ እምነታቸው መሆኑን አቶ ስዩም ወልደገብርኤልና ተናግረዋል። ህዝቡም ሰላሙን ለመጠበቅ ዘብ መቆም አለበት ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም