ዓለም አቀፍ ድርጅቶቹ የኢትዮጵያን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የመከላከል ተግባር የሚያግዝ ፕሮጀክት ይፋ አደረጉ

55

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 19/2012 ( ኢዜአ) ኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል እየከወነች ያለውን ተግባር ለመደገፍ ዋተር ኤይድ፣ የህጻናት አድን ድርጅትና ዩኒሴፍ አዲስ ፕሮጀክት ይፋ አደረጉ።

ድርጅቶቹ ከኮቪድ-19 ጋር በተገናኘ በንጽህና አጠባበቅና በባህሪ ለውጥ ማምጣት በጥምረት የሚሰሩበትን አዲስ ፕሮጀክት ነው ይፋ ያደረጉት።

ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያ መንግስት የኮሮና ወረርሽኝ ስርጭትን ለመቆጣጠር የሚያደርገውን ጥረት ለመደገፍ፣ ለንጽህና አጠባበቅና የባህሪ ለውጥ ይሰራል።

የመገናኛ ብዙሃንና የእርስ በእርስ ተግባቦት ዘመቻን በመጠቀም በንጽህና አጠባበቅ ላይ ለውጥ ለማምጣት ያለመ ነውም ተብሏል።

ፕሮጀክቱ በከተማ አስተዳደሮችና በሁሉም ክልሎች የሚተገበር ሲሆን በአስር ሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ከንጽህና አጠባበቅ ጋር ተያያዥነት ያላቸው መልክቶችን ተደራሽ ያደርጋል።

የማቆያ ማዕከላትና የጤና ተቋማትን ንጽህና ለመጠበቅ ሳኒታይዘርና አልኮልም ያሰራጫል ተብሏል።

የወረርሽኙን ስርጭት ለመቀነስ ሕዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች በተደጋጋሚ እጅን በሳሙናና ውሃ በደንብ የመታጠብን ግንዛቤ የመፍጠር ስራም ይከናወናል።

በተጨማሪም የንጽህና መጠበቂያ ችግር በከፋባቸው አካባቢዎች አስፈላጊውን ግብዓት ማሟላት በፕሮጀክቱ ተካቷል።

ኮሮናቫይረስን ጨምሮ ተላላፊ በሽታዎችን በዘላቂነት ለመከላከል የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ በማከፋፈል “ፅዱ ኢትዮጵያ”ን ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረትም ያግዛል ነው የተባለው።

በኢትዮጵያ የዋተር ኤይድ ዳይሬክተር ያዕቆብ መተና እንዳሉት ማኅበረሰቡን ኮቪድ-19ን ከመሰሉ ተላላፊ በሽታዎች ለመከላከል ውሃ፣ ንጽህናና የንጽህና አጠባበቅ የመጀመሪያ መከላከያዎች ናቸው።

በመሆኑም ዋተር ኤድ የኢትዮጵያ መንግስት በውሃ፣ ንጽህናና የንጽህና አጠባበቅ ልማት እየሰራ ያለውን ተግባር ያግዛል ብለዋል።

የሕጻናት አድን ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ኢኪን ኦጉቱጉላሪ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ የሚተገበረው የወረርሽኙ ስርጭት ከፍተኛ በሆነባቸው አካባቢዎች በመሆኑ መንግስት ለመከላከል የሚያደርገው ጥረት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

ለሚካሄደው የባህሪ ለውጥ ዘመቻ ዘጠኝ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትን በአጋርነት አካቷልም ብለዋል።

የስደተኞች መጠለያዎች፣ የጠረፍና የገበያ አካባቢዎችን ተደራሽ ማድረግ የእርስ በእርስ ተግባቦት የባህሪ ለውጥ ዘመቻው አካል እንደሆነም ተነግሯል።

ፕሮጀክቱ በቪዲዮ ኮንፍረንስ ይፋ ሲደረግ የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ፣ የጤና ሚኒስቴርና የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባለሙያዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም