የሕክምና ግብዓቶችና የኢንፌክሽን መከላከያ ቁሳቁስ ለማሟላት እየተሰራ ነው - ጤና ሚኒስቴር

69

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 19/2012 ( ኢዜአ) ለጤና ተቋማት የሕክምና ግብዓቶችና የኢንፌክሽን መከላከያ ቁሳቁስ ለሟሟላት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ገለጹ።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ ለጤና ተቋማቱ በግዥ አልያም በዕርዳታ የሚገኙ የሕክምና መሳሪያዎችና ግብዓቶችን የማሰባሰብ ሥራው ተጠናክሯል ብለዋል።

በተለይም በጽኑ ሕሙማን ክትትል ለሚገኙ የኮቪድ-19 ታካሚዎች የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ የሕክምና ግብዓቶችን ለማሟላት አጽንኦት መሰጠቱን ገልጸዋል።

ያም ሆኖ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የግብዓት እጥረትና አንዳንድ አምራች አገራት ምርታቸውን ወደ ሌሎች አገራት መላክ ማቆማቸው ጫና አሳድሯል ነው ያሉት።

ይህን ክፍተት ለመሙላት በተለይም የአገር ውስጥ አምራች ኩባንያዎች በስፋት ወደ ምርት ሥራ እንዲገቡ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በጤና ተቋማት ከኮሮና ውጭ መደበኛ የጤና አገልግሎት አሰጣጡ በተሟላ መልኩ እንዲሄድ አስፈላጊ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል።

የላቦራቶሪ ማዕከላትን የማስፋት ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉንና ንክኪ ያላቸውን ሰዎች የመለየትና የመመርመር ሥራም መጠናከሩን ገልጸዋል።

በቅርቡ ከተሻሻሉት መመሪያዎች መካከል በቤታቸው መቆየት የሚችሉ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች በመመሪያው መሰረት ገቢራዊ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይህም የመኖሪያ ቤታቸውና ሌሎች አስቻይ ሁኔታዎች መኖራቸው በጤና ባለሙያዎች ከተረጋገጠ በኋላ በቤታቸው እንዲቆዩ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ነገር ግን ያሉበት ሁኔታ ይህንን የማይፈቅድ ከሆነ ወደ ማቆያ እንዲገቡ ይደረጋል ብለዋል።

ግለሰቦች በማቆያ ማዕከል ከተቀመጠላቸው ጊዜ ገደብ በተጨማሪ በሚደረግላቸው ተደጋጋሚ ምርመራ ቫይረሱ ካለባቸው ቆይታቸው ሊራዘም ይችላል ነው ያሉት።

በቅርቡ በተሻሻለው መመሪያ መሰረትም ከውጭ የሚገቡ መንገደኞችን ማስተናገድ መጀመሩን ገልጸው በሂደቱ የሚነሱ ቅሬታዎች እንደሚፈቱም ተናግረዋል።

ዶክተር ሊያ ወረርሽኙን ለመከላከል እያንዳንዱ ግለሰብ የሚያደርገውን ጥንቃቄ እንዲያጠናክር፤ ተጓዳኝ በሽታ ያለባቸውም ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 5 ሺህ 425 የደረሰ ሲሆን 89 ሰዎች በቫይረሱ ምክንያት ለሞት ተዳርገዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም