የግብር ግዴታቸውን በወቅቱ እንደሚወጡ በደብረ ብርሃን ከተማ ግብር ከፋይ ነጋዴዎች ገለጹ

79
ደብረብርሃን ሀምሌ 2/2010 የሚጠበቅባቸውን የገቢ ግብር በታማኝነት በመክፈል ግዴታቸውን በወቅቱ እንደሚወጡ በደብረ ብርሃን ከተማ ግብር ከፋይ ነጋዴዎች ገለጹ፡፡ ደብረ ብረሃን ከተማን ጨምሮ በሰሜን ሸዋ ከደረጃ "ሐ " ግብር ከፋዮች ከ49  ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ እንቅስቃሴ መጀመሩን የዞን ገቢዎች ጽህፈት ቤት አመልክቷል፡፡ በከተማው የቀበሌ ስምንት ነዋሪ አቶ ሽኩር ሙሳ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት በተሰማሩበት የሸቀጣሸቀጥ ንግድ የሚጠበቅባቸውን ግብር በወቅቱና በታማኝነት በመክፈል ልማትን ለማፋጠን የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡ በሚሰሩት ልክ የተጣለባቸውን 5 ሺህ 839 ብር በወቅቱ መክፈላቸውን ጠቁመው፤ ሌላው ግብር ከፋ ነጋዴም የሚሰበሰበው ግብር ተመልሶ ለልማት የሚውል መሆኑን በመገንዘብ ግብርን በተገቢው መክፈል እንዳለበት አመልክተዋል። " ባለፈው ዓመት ከአቅሜ በላይ 9 ሺህ ብር ግብር ተጥሎብኝ ባቀረብኩት ቅራኔ መስረት ወደ 3 ሺህ 608 ብር ዝቅ ብሎልኝ በወቅቱ ክፍያለሁ " ያሉት ደግሞ በከተማው በፎቶ ማንሳት ስራ የተሰማሩት አቶ ያሬድ ጥኡመልሳን ናቸው፡፡ በተያዘው በጀት ዓመትም እንዳለፈው ዓመት ሁሉ  የተጣለባቸውን የግብር ክፍያ በመጀመሪያው ቀን መፈጸማቸውንና  በቀጣይም ይህንኑ  ልምዳቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡ የዞን ገቢዎች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳንኤል ንጉሴ እንዳመለከቱት በሰሜን ሸዋ ደብረ ብርሃን ከተማን ጨምሮ  35 ሺህ 577  የደረጃ "ሐ" ግብር ከፋይ ነጋዴዎች ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ግብር ከፋዮች ከ49  ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረው በእቅድ የተያዘው ይህንን ገቢ ለማሳካት  132 ጊዜያዊ የግብር መሰብሰቢያ ጣቢያዎች መዘጋጀታቸውን አስረድተዋል፡፡ በዚህም ተገልጋዮች በአግባቡ እንዲሰተናገዱ የወረፋ ካርድና ድንኳን ተሰናድቶ እየተሰራ ነው ፡፡ በየደረጃው ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር የንቅንቄ መድረኮች በማሰናዳትና ግንዛቤ በመፈጠሩ ከሐምሌ 1 ጀምሮ ለ30 ቀናት የነበረውን የጊዜ ገደብ በመጀመሪያዎቹ አስር ቀናት ውስጥ ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡ ባለፈው የበጀት  ዓመት  ከ29 ሺህ በሚበልጡ የደረጃ" ሐ " ግብር ከፋዮች 48 ሚሊዮን ብር  በላይ መሰብሰቡን ያስታወሱት አቶ ዳንኤል" ዘንድሮ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የተሻለ ለመፈጸም በቂ ዝግጅት ተድርጓል "ብለዋል፡፡ የንግዱ ማህበረሰብም የተጣለበትን ግብር በታማኝነትና በወቅቱ በመክፈል ለዞኑ ልማት የድርሻውን እንዲወጣም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በዞኑ በ2011 በጀት ዓመት ከደረጃ " ሐ" እና ከሌሎችም ምድብ ግብር ከፋዮች ከ895 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ መታቀዱን ጽህፈት ቤቱ አመልክቷል፡፡            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም