የአፍሪካ አገራት ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነቱ ሥራ ላይ እንዲውል የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል ተባለ

56
አዲስ አበባ ግንቦት 3/2010 የአፍሪካ አገራት አህጉር አቀፍ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነት ሥራ ላይ እንዲውል የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ። ስምምነቱ እውን በሚሆንበት ጉዳይ ላይ የሚመክር ጉባኤ ዛሬ በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን አዳራሽ መካሄድ የጀመረ ሲሆን ለአምስት ተከታታይ ቀናት እንደሚቆይ ተገልጿል። ጉባኤው የአፍሪካ የፋይናንስ፣ ዕቅድና ልማት ሚኒስትሮች የሚሳተፉበት ሲሆን በባለሙያዎች ደረጃም ጉባኤው ዛሬ ተጀምሯል። ግብርናና መዋቅራዊ ለውጥ፣ የመሰረተ ልማት ፋይናንስ፣ ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን መከላከል የመወያያ አጀንዳዎቹ ናቸው። የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነትን በሩዋንዳ ዋና ከተማ ኪጋሊ 44 የአፍሪካ አጋራት መፈረማቸው ይታወሳል። ስምምነቱ ሥራ ላይ እንዲውል ቢያንስ 22 አገራት ማጽደቅ እንዳለባቸው ተቀምጧል። በትላንትናው ዕለትም ጋናና ኬኒያ ስምምነቱን በማጽደቅ ቀዳሚ መሆን ችለዋል። የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸሀፊ ሚስ ቬራ ሶንግዌ  እንደገለጹት፤ ስምምነቱን ተግባራዊ ማድረግ የኢኮኖሚ ዕድገቱን አማራጭ ለማስፋት፣ በኢንዱስትሪ ዘርፍና ልማት በአፍሪካ የሚጠበቀው ብልጽግና እንዲመጣ አዎንታዊ ሚና ይጫወታል። ''የአፍሪካ አገራት በንግድ በመተሳሰር በኩል ያሉበት ደረጃ ዝቅተኛ ነው'' ያሉት ሚስ ቬራ አገራቱ ስምምነቱ መሬት እንዲወርድ በማድረግ ከሚገኘው ትሩፋት ሊጠቀሙ ይገባል ብለዋል። በአፍሪካ 80 በመቶ የሚሆነው ንግድ በጥቃቅን፣ መካከለኛና ኢንተርፕራይዝ ላይ የተመሰረተ እንደመሆኑ የስምምነቱ እውን መሆን ከዘርፉ የሚገኘው ጥቅም እንዲጨምር ያደርጋል ነው ያሉት። ስምምነቱ አገራት ከዕቃዎች ላይ የሚያገኙት ታክስ ገቢ እንዲቀንስ ያደርጋል የሚል ስጋት መኖሩን አብራርተው በገቢው ላይ ያን ያህል አሉታዊ ተጽእኖ አይኖረውም ሲሉ አስረድተዋል። በኮሚሽኑ የኢትዮጵያ ቋሚ ተወካይ አምባሳደር ወይንሸት ታደሰ በበኩላቸው ስምምነቱ ወሳኝና ወቅታዊ መሆኑን ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ስምምነቱ በሚያስገኛቸው ጠቀሜታዎች ላይ የበለጠ ግንዛቤ ለመፍጠር ብዙ መስራት ይጠበቃል ብለዋል። በኮሚሽኑ የባለሙያዎች ኮሚቴ ሊቀ-መንበር ሚስተር ማያሲኔ ካማራ እንደተናገሩት የአጀንዳ 2063 ግቦች እንዲሳኩ ለወጣቶችና ሴቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ወሳኝ ሚና አለው። ነጻ የንግድ ቀጣና ስምምነቱም ለሥራ ዕድል ፈጠራ የራሱን ሚና የሚጫወት በመሆኑ ለተግባራዊነቱ ሁሉም የአፍሪካ አገራት በቁርጠኝነት እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ አቅርበዋል። በተለይም የአፍሪካ አገራት የሚልኳቸው ምርቶች እሴት የተጨመረባቸው ባለመሆናቸው ገቢው ዝቅተኛ ነው ያሉት ሊቀ-መንበሩ ስምምነቱ በዚህ በኩል የሚታዩ ችግሮች እንዲፈቱ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል። የአፍሪካ ኢኮኖሚ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2017 የ 3 ነጥብ 1 በመቶ ዕድገት ያስመዘገበ ሲሆን በዓለም ከምስራቅና ደቡብ እስያ በመቀጠል ፈጣን ዕድገት እያስመዘገበ መሆኑ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም