የመኸር ዝናብን በመጠቀም ማሳዎቻችንን በተለያዩ ሰብሎች እየሸፈንን ነው–የትግራይ አርሶ አደሮች

87

መቀሌ ሰኔ 19/2012 ( ኢዜአ) በአሁኑ ወቅት እየጣለ ያለው የተስተካከለ የዝናብ ስርጭት ተጠቅመው በዘንድሮው የመኽር አዝመራ ምርታቸውን ለማሳደግ ማሳዎቻቸውን በተለያዩ ሰብሎች በመሸፈን ላይ እንደሚገኙ የትግራይ ክልል አርሶአደሮች ገለፁ ።

የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ በበኩሉ በመኽር አዝመራ ዝግጅት ስራው እስከ አሁን ድረስ 224 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች መሸፈናቸውን ገልጿል።

በትግራይ ምስራቃዊ ዞን በአፅቢ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ሃይለስላሴ ተስፋይ እንዳሉት ያላቸው አራት ጥማድ ማሳ በተደጋጋሚ ማረሳቸውን ተናግረዋል።

የዘንድሮ የክረምት ዝናብ  ቀድሞ መጣል በመጀመሩና ለሰብሎች ተስማሚ በመሆኑ በሁለት ጥማድ ማሳ ላይ ገብስ መዝራታቸውን ገልጸዋል።

የተቀረው ሁለት ጥማድ ደግሞ በስንዴ ዘር ለመሸፈን በዝግጅት ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ከአንድ ወር በፊት የጀመረው ዝናብ  በሁለት ጥማድ መሬት ላይ የዘሩትን ማሽላ በቂ እርጥበት በማግኘቱ በጥሩ ቁመና ላይ እንደሚገኝ የተናገሩት ደግሞ በትግራይ ማእከላዊ ዞን የአሕፈሮም ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ፀጋይ ክንፈ ናቸው።

በአካባቢያቸው የሚጥለው ዝናብ ወደ ማሳቸው ለማስገባት የጎርፍ መቀልበሻ መስራታቸውና እርጥበትን የሚያከማቹ ጉድጓዶችን በመቆፈራቸው በአሁኑ ወቅት በቂ ውሃ እየሰረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

በትግራይ ደቡባዊ ምስራቅ ዞን የእንደርታ ወረዳ አርሶ አደር አሰፋ ግርማይ በበኩላቸው በምግብ ራስን ለመቻል የሚያግዝ የማሳ ለምነትን የማጎልበትና እርጥበትን የማከማቸት ክህሎት በቪድዮ ኮንፈረንስ የተደገፈ ስልጠና ወስደዋል።

በተጨማሪም በመስመር የመዝራትና በማዳበሪያ አጠቃቀም ላይም ተመሳሳይ ስልጠና በመውሰድ ከሌሎች የአካባቢያቸው አርሶ አደሮች ጋር በመሆን እየተገበሩት መሆናቸውን አርሶ አደር አሰፋ አስታውሰዋል።

ተጨማሪ ዝናብ ሲዘንብ ማሳቸው እርጥበት እንዲቋጥር የተለያዩ ተግባራት እያከናወኑ  መሆናቸውን ተናግረዋል።

በትግራይ ደቡባዊ ዞን በእንዳመኾኒ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር አለምፀሃይ ረዳኢ እንዳሉትም በበጋ ወቅት ያዘጋጁትን ባህላዊ ፍግ ወደ ማሳቸው በመጨመር ሁለት ጥማድ ማሳቸው በስንዴ ምርጥ ዘር ሸፍነዋል።

የተሻለ ምርት ለመሰብሰብ ከግብርና ባለሙያዎች ያገኙትን ስልጠና ተግባራዊ እያደረጉ መሆናቸውም ተናግረዋል።

የትግራይ ክልል ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ክፍሎም አባዲ እንደገለፁት ካለፈው ሚያዚያ  ጀምሮ በክልሉ የተሻለ ዝናብ በመዝነቡ አርሶ አደሮች ቀድመው ማሳቸውን አርሰውና አለሳልሰው በተለያዩ ሰብሎች እየሸፈኑ ነው።

በክልሉ የተካሄደውን የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራን ተከትሎ አርሶ አደሮች ማሳን የማለሳለስ፣ የጎርፍ መቀልበሻ ቦዮችን የመገንባት እና እርጥበትን ለማከማቸት የሚያስችሉ ሌሎች የውሃ ስራዎችን ሲያከናውኑ ቆይተዋል ብለዋል።

በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ቀድመው የማሽላና የበቆሎ ሰብሎችን የተዘሩ ሲሆን የብርእ ሰብሎች ደግሞ በመዘራት ላይ እንደሚገኙ አቶ ክፍገ  ገልጸዋል።

እስከ አሁን ድረስም በክልሉ ውስጥ ከ224 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በተለያዩ ሰብሎች ተሸፍኗል ብለዋል።

በትግራይ ክልል በዘንድሮው የመኸር ወቅት አንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች እንደሚሸፈን መገለጹ ይታወሳል።