በኮሮና ምክንያት ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የማህበረሰብ ክፍሎች ድጋፎችን እያደረግን ነው-- የሐይማኖት ተቋማት

51

ሰኔ 19/2020 (ኢዜአ) የሐይማኖት ተቋማቱ ዘርን ጾታንና እምነትን ሳይለዩ ለኮሮና ተጋላጮች ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙ አስታወቀዋል፡፡

በተለይም የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎች ላይ ትኩረት አድርገው እየሰሩ እንደሚገኝ ነው ያስታወቁት፡፡

ኮቪድ -19  በኢትዮጵያ መከሰቱ ከታወቀ ጀምሮ  መንግሥታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከሚያደርጉት ድጋፍ በተጨማሪ የሐይማኖት ተቋማትም በበሽታው ተጋላጭ የሆኑትንና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች በማገዝ ላይ ይገኛሉ፡፡

ተቋማቱ ከሚያደርጉት ድጋፍ በተጓዳኝ የግንዛቤ ማስጨበጥ ተግበራትን ትኩረት አድርገው እንደሚሰሩም ነው የሚገልጹት፡፡

 ኢዜአ ያነጋገራቸው በሦስት የሀይማኖት ተቋማት ስር ያሉ  ኮሮናን ለመከላከል በሚደረገው እንቅስቃሴ ግብረ ኀይል በማቋቋም ተደራሽ ለሆኑባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ሁሉ የድጋፍ ተግባራትን  እያከናወኑ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ይልቃል ሽፈራው እንደሚሉት  ቤተክርስቲያኗ ኮቪድ- 19 የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ከባለሙያዎች የተውጣጣ  ግብረሓይል አቋቁማለች፡፡

በዚህም ለመንግሰት ከተደረገው የ3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ውጪ ፣ ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በሚሆን መልኩ  የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ፤ የገንዘብና የደረቅ ምግብ ድጋፎች ተደርገዋል፡፡

ድጋፉም ዘርን ጾታንና እንዲሁም የሀይማኖት ሁኔታን ሳይለይ እየተደረገ እንደሚገኝ በመግለጽ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በሽታው የቤተክርስቲያኗን  አገልጋዮች ቢያጠቃ ከቤተክርስቲያኗ ስርዓት አንጻር ሕክምና  እንዴት ማግኘት እንዳለባቸው ከህክምና ባለሙያዎች ጋር ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

በሌላ በኩል በሽታው የሚያደርሰውን ስነ ልቦናዊ ጫና ለመከላከል 73 የዘርፉ ባለሙያች ለተከታታይ 4 ወራት የስነ ልቦና ህከምና ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ገልጸው፣ በጾታዊ ጥቃት እየደረሰ ያለውን ችግር ለመከላከልም እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ተናግረዋል ፡፡

በየጊዜው ከበሽታው ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ  ነገሮችን  ከኢትዮጵያ የሐይማኖት ተቋማት ጋር በመሆን ለህዝበ ሙስሊሙ እያደረሱ እንደሚገኝ ያስታወቁት ደግሞ  በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የኮሮና መከላከል ግብረ ሃይል ጸሃፊ ኢንጂነር አንዋር ሙስጠፋ  ናቸው፡፡

በተለይም ባለፈው የረመዳን የጾም ወቅት ተጋላጮችን በመደገፍ እና ግንዛቤ በማስጨበጥ  በኩል ሰፊ ስራዎች መከናወናቸውን አንስተው ከጤና ጥበቃ ባለሙያዎች ጋር በመሆን  ሀይማኖታዊ ብያኔዎች (ፈቱዐ) መሰጠታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ብያኔዎቹም ህዝበ ሙስሊሙ  ሃይማኖታዊ ስርዓቶችን ኮሮናን ከመከላከል ጎን ለጎን በቤቱ ሆኖ የሚፈጽምበትን መንገድ  የተመለከተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በኮቪድ 19 ኮሮና ወቅት የቀብር ስነ ስርኣት እንዴት መከናወን እንዳለበት  የሚያመለከት ተጨማሪ ፈቱዐ መዘጋጀቱንም ነው የገለጹት፡፡

መጅሊሱ  የአወሊያ ኮሌጅ ሁለገብ ማዕከልን ለለይቶ ማቆያነት መስጠቱን አስታውሰው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎቹና የድገፍ ተግባራቱ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ባማከለ መልኩ እየተከናወኑ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡

ህዝበ ሙስሊም ይህንን ችግር ከጎረቤቱ ጋር ተሳስሮ መቅረፍ እንደሚገባውም  አስረድተዋል፡፡

ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያገለግሉ ድንኳኖችን ፣ የንጽህና መጠበቂያ ሳኒታይዘር፣  የህመም ማስታገሻ መድሃኒቶችን  እንዲሁም ግንዛቤ ለማስጨበጥ ሚረዱ መሳሪያዎችን በመግዛት ማሰራጨቱን ያስታወቀው ደግሞ የኢትዮጵያ የካቶሊክ  የእርዳታ ድርጅት ነው፡፡

የደርጅቱ  ምክትል የፕሮግራም አስተባባሪ  የሆኑት  ቤተል መክብብ  እንዳሉት የድጋፍ ስራዎቹ ተገላጭ የሆኑ ሰዎችን ያማከሉ ሲሆን መሰረታዊ ፍላታቸውን የሚያሟሉበትን የገንዘብ ድጋፍም ያካተተ ነው፡፡

ባለሁት ሶስት ወራትም  ከ77 ሺህ ሜተሪክ  ቶን በላይ የምግብ አቅርቦት በተለያዩ ቦታዎች ላይ መደረጉን አስረድተው ለ2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሰዎች ተደራሽ መደረጉን አንስተዋል ፡፡

ለችግሩ የበለጠ ተጋላጭ የሆኑ ነፍሰ ጡር እና  አጥቢ እናቶችን እንዲሁም አካል ጉዳተኞች በዋናነት የደጋፉ ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ትምህርት ቤቶችና ተቋማት ለለይቶ ማቆያነት መሰጠታቸውን የገለጹት ሃላፊዋ ፤ ኮሮና ከፍተኛ  ኢኮኖሚያዊ  ጉዳት አድርሶባቸው የሚያልፈውን የህብረተሰብ ክፍሎች ለማቋቋም እቅድ  መነደፋቸውን አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም