ባለፉት 3 ወራት ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ180 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል

46

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 19/2012 ( ኢዜአ) ባለፉት ሶስት ወራት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከ180 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ከኅብረተሰብ ተሳትፎ መገኘቱን የግድቡ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ገለጸ።

ገቢው የኮሮና ቫይረስ ኢትዮጵያ ውስጥ መግባቱ ከተረጋገጠበት ካለፈው መጋቢት እስከ ግንቦት መጨረሻ ድረስ የተሰበሰበ መሆኑ ተገልጿል።

የጽህፈት ቤቱ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም ለኢዜአ እንደገለጹት ኅብረተሰቡ ለሕዳሴ ግድቡ የሚያደርገው ተሳትፎ እየጨመረ ነው።

ለዚህ ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ ከኀብረተሰቡ ተሳትፎ የተገኘውን ከ180 ሚሊዮን 950 ሺህ ብር በላይ ገቢ ለአብነት አንስተዋል።

ገቢው በተለይ ከ"8100 A" እና ከቦንድ ግዥ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ-ግብሮች መገኘቱንም ገልጸዋል።

ዓለም አቀፍ ችግር በሆነው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ ሰፊ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ-ግብሮች ማካሄድ በማይቻልበት ሁኔታ ይህ ገቢ ከኅብረተሰቡ መገኘቱ የሚያበረታታ እንደሆነም ነው የገለጹት።

ይህም ሕዝቡ ለሕዳሴ ግድቡ እውን መሆን ያለውን ቁጭትና ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ አክለዋል።

ኅብረተሰቡ ግድቡን ለማጠናቀቅ በሚደረገው ጥረት የኮሮናቫይረስ ተጽዕኖ ሳይገድበው ጤናውን እየጠበቀ ተሳትፎውን ይበልጥ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።

የአገሪቷን ሠላምና አንድነት በማስጠበቅና ሉዓላዊነትን በማጠናከር የመደጋገፍ ስሜቱ መቀጠል እንዳለበትም ተናግረዋል።

እስካሁን ሕዝቡ ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ በማዋጣት ለፕሮጀክቱ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑ ተነግሯል።

የግንባታ አፈጻጸሙ 74 በመቶ የደረሰው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በመጪው ሐምሌ የውሃ ሙሌት እንደሚጀመርም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም