የጋምቤላ ህዝብ የህዳሴ ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል - አቶ ኡሞድ ኡጁሉ

59

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 19/2012 ( ኢዜአ) ''የጋምቤላ ህዝብ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል'' ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ የህልውና መሰረት መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ በግድቡ ግንባታ ዙሪያ በሚከናወኑ ተግባራት የኢትዮጵያ ህዝብ የሚፈተንበት ጉዳይ ነው።

ፈተናውን ለማለፍ ህዝቡ በትጋት በመስራት በገንዘብ፣ በሞራልና በጉልበት ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል።

የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅ በሌሎች ክልሎች የሚካሄዱ የንቅናቄ ስራዎች በሙሉ በጋምቤላ ክልልም እየተካሄዱ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

እንደ ርዕሰ መስተዳድሩ ገለጻ፤ በተለያዩ አካላት በኩል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማስተጓጎል የሚደረገውን ጥረት የጋምቤላ ህዝብ ይቃወማል።

''ግድቡ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የህልውና መሰረት ነው'' ያሉት አቶ ኡሞድ፤ ግንባታው እስከሚጠናቀቅ ድረስ የጋምቤላ ክልል የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

“በአሜሪካ መንግስት የሚታየው አድሎዊ አሰራርን የክልሉ መንግስትና ህዝብ ይቃወመዋል” ብለዋል። 

የዘጠኙ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድር ከሳምንት በፊት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ያለበትን ደረጃ እንደጎበኙ ያስታወሱት አቶ ኡሞድ፤ ግንባታውን ለማጠናቀቅ የተጠናከረ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የግድቡ ግንባታ 74 በመቶ የደረሰ ሲሆን በዚህ ክረምት የውኃ ሙሌት ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል።

የግድቡ ውሃ የሚተኛበት አንድ ሺህ ሄክታር መሬት የደን ምንጣሮ ስራ የፊታችን እሁድ ሰኔ 21 ቀን 2012 ዓ.ም ይጀመራል። 

በደን ምንጣሮ ስራ ላይ የሚሳተፉ 61 ኢንተርፕራይዞች ወደ ስፍራው የገቡ ሲሆን 32 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በጀት ተመድቧል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም