የኢትዮጵያ ፌዴራሊስት ኃይሎች ጥምረት ሕወሓትን በይፋ ከጥምረቱ አባልነት ሰረዘ

54

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ፌዴራሊስት ኃይሎች ጥምረት ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) እና የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኅብረት (ኢዴኅ)ን ከጥምረቱ የሥምምነት ዓላማዎች ውጪ በመንቀሳቀሳቸው ከአባልነት ሰርዣቸዋለሁ አለ።

ጥምረቱ በትናትናው ዕለት አራተኛ መደበኛ ጉባዔውን ባካሄደበት ወቅት ሕወሓትን ከጥምረቱ አባልነት መሰረዙን ለኢዜአ ማስታወቁ የሚታወስ ነው።

በዛሬው ዕለትም በሰጠው መግለጫም ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) እና የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኅብረት (ኢዴኅ)ን በይፋ ከጥምረቱ ስለማሰናበቱ አስታውቋል።

በዚሁ ጊዜ የጥምረቱ አባል የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በሰጡት አስተያየት እንዳሉት ሕወሓት የጥምረቱን ኃይል አባል የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳሻው የማዘዝ ፍላጎት ማሳየቱ ትክክል አይደለም ተብሏል።

በጥምረቱ ውስጥ የታቀፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረቱ ባወጣቸው ዓላማዎች ብቻ መንቀሳቀስ ሲኖርባቸው ሕወሓት ግን ከጥምረቱ ዓላማ ውጪ ሲንቀሳቀስ ነበርም ተብሏል። 

በተጨማሪም ጥምረቱ ጠቅላላ ጉባዔውን ለማካሄድ ከአንዴም ሁለት ጊዜ ጥሪ ቢያቀርብላቸው ጥሪውን ሳይቀበሉ በመቅረታቸው መሰናበታቸው ተገቢ ነው ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።

በተጨማሪም "ሕወሓት የጥምረቱን አባል የፖለቲካ ፓርቲዎች ለመከፋፈልና ጥምረቱን ለመበታተን ሲሰራ ነበር" ሲሉም ክስ ሰንዝረዋል።


ሕወሓት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እያለ ምርጫ ለማካሄድ መቃዱም ከጥምረቱ እንዲሰናበት ሌላ ተጨማሪ ምክንያት ነው ተብሏል።

የጥምረቱ ሊቀመንበር አቶ ደረጀ በቀለ በዚሁ ወቅት እንዳሉትም ሕወሓት በዚህ ኮቪድ-19 አስጊ በሆነበት ወቅት ምርጫ አካሂዳለሁ ማለቱ ተቀባይነት የለውም።

የሕወሓት ምርጫ አካሂዳለሁ ማለት ጥምረቱ ይዞ ከሚንቀሳቀሰው አጃንዳ ውጪ በመሆኑም ፓርቲው ከጥምረቱ አባልነት ማፈንገጡን ያሳየ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

በዚሁ መሠረት ሁሉም የጥምረቱ አባል የፖለቲካ ፓርቲዎች በመስማማታቸው በዛሬው ዕለት ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) እና በተደጋጋሚ ጠቅላላ ጉባኤ ተጠርቶ አልተገኘም፣ የአፍራሽ ተልዕኮም ተባባሪ ሆኗል የተባለው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኅብረት (ኢዴኅ) ከጥምረቱ በይፋ መሰናበታቸው ተገልጿል።

ጥምረቱ ዛሬ ይፋ ባደረገው መሠረት በጥምረቱ 27 የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖራቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም