በስልጤ ዞን በበልጉ ወቅት ከለማው መሬት ከአምስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተሰበሰበ

325

ሆሳዕና፣ ሰኔ 18/2012 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል ስልጤ ዞን በዘንድሮ የበልግ ወቅት ከለማው የእርሻ መሬት ከአምስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያገለፀ።

ምርቱ የተሰበሰበው  በወቅቱ  ከለማው ከ49 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ ነው።

የተሰበሰበው ምርት ድንች፣ በቆሎና የጥራጥሬ  ሰብል መሆኑን የመምሪያው ኃላፊ አቶ ፃዲቅ አህመዲን ለኢዜአ  ተናግረዋል።  

ምርቱ የተሰበሰበት መሬት ለተያዘው የመኸር አዝመራ ወቅት ጭምር ለማዋል  የኮሮና ወረርሽኝ በግብርና ልማት ላይ ተፅዕኖ እንዳይፈጥር  ዝግጁ መደረጉን አመልክተዋል።

በዚህ የምርት ወቅት  54 ሺህ 700  ሄክታር  መሬትን በዋና ዋና ሰብል ለማልማት ታቅዶ ወደ ስራ  መገባቱን ገልጸው” አርሶ አደሩም ጊዜውን በአግባቡ በመጠቀም የእርሻ ስራውን እያከናወነ ይገኛል “ብለዋል።

እቅዱን ለማሳካት 214 ሺህ ኩንታል ማዳበሪያና ምርጥ ዘር  ለማሰራጨት ከታቀደው ውስጥ  እስካሁን 75 በመቶ   ለአርሶ አደሩ መድረሱን አስታውቀዋል።

ከወረርሽኙ ጋር ተያይዞ በዞኑ 218 ሺህ የህብረተሰብ ክፍሎች ለምግብ ዋስትና ችግር ተጋላጭ እንደሚሆኑ  በተካሄደው የዳሰሳ ጥናት መለየቱን ጠቁመዋል።

ችግሩን ለመከላከል በተለያየ አደረጃጀት የተያዘ 8 ሺህ 752  ሄክታር ያለማ  መሬት ልማት ውሰጥ ለማስገባት አቅጣጫ መያዙን አብራርተዋል።

በዞኑ ምዕራብ አዘርነት በርበሬ ወረዳ የሙጎ ቀበሌ አርሶ አደር ሻፊ ቀድራላ በሰጡት አስተያየት በበልግ ወቅት  ካለሙት አንድ ሄክታር ማሳቸው  62 ኩንታል ድንች ምርት በመሰብሰብ ለሽያጭ እያቀረቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ምርት በተሰበሰበበት  ማሳ ላይ በተያዘው የመኸር ወቅት  በስንዴ ሰብል ለማልማት የቀረበላቸውን ግብዓት ተጠቅመው እየሰሩ እንደሚገኙም አመልክተዋል።

ግማሽ ሄክታር መሬት ላይ ካለሙት በቆሎ 50 ኩንታል ምርት በመሰብሰብ  ለሽያጭ መቅረባቸውን የገለጹት ደግሞ በሁልባረግ ወረዳ የዋጮቢሶ ቀበሌ አርሶ አደር በድሩ ከማል ናቸው።

አርሶ አደሩ  እንዳሉት የግጦሽ እጥረት እንዳያጋጥማቸውም የበቆሎ  አገዳውን በማከማቸት ለከብቶቻቸው መኖ እያዋሉ ነው።

በስልጤ ዞን  በ2012/2013 የምርት ዘመን ከ260 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ  ስንዴ፣ ጤፍ፣ ገብስ፣ በቆሎና ስራ ስር ለማልማት ታቅዶ እየተሰራ ነው።

የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ እንዳመለከተው   በስልጤ አከባቢ  የበልግ ወቅት ከየካቲት እስከ ግንቦት መኸር ደግሞ ከሰኔ እስከ ነሐሴ መጨረሻ  ይቆያል።