ተፎካካሪ ፓርቲዎች በሕዝብና ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ ተመለከተ

55

ጋምቤላ፣ ሰኔ 18/2012 (ኢዜአ) ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የዓላማ ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው በሕዝብና ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ተባብረው ሊሰሩ እንደሚገባ ተመለከተ።

ብልፅግናን ጨምሮ በጋምቤላ ክልል የሚገኙ አራት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች የአረንጓዴ አሻራ ቀንን ምክንያት በማድረግ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አካሂደዋል።

የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ሥራአስፈጻሚ አባል አቶ ዑሞድ ኡጁሉ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የኮሮና ወረርሽኝን በመከላከል፣ በአረንጓዴ አሻራ ልማትና በሌሎችም ክልላዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተባብረው ሊሰሩ ይገባል።

የፖለቲካ ልዩነቶችን ወደ ጎን  በመተው በሕዝብና ሀገር ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ በአንድነት መሥራት እንዳለባቸውም አመልክተዋል።

"የፖለቲካ ዓላማን ማራመድ የሚቻለው ሕዝብና ሀገር ሲኖር ነው" ያሉት አቶ ዑሞድ በክልሉ የሚገኙ ፓርቲዎች በአረንጓዴ አሻራ ልማት ዙሪያ ላሳዩት ተሳትፎ ምሥጋቸውን አቅርበዋል።

ባለፈው ዓመት የተተከሉ ችግኞች በተደረገላቸው እንክብካቤ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ መመልከታቸውን ገልጸው ዘንድሮም በቀጠለው በዚሁ መርሃ ግብር ላይ   ህዝቡ እንዲሳተፍ መልዕክታቸውን አስላልፈዋል።

በችግኝ ተከላው የተሳተፉት የጋምቤላ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ጋሕነን) ሊቀመንበር አቶ ፒተር ዓማን በበኩላቸው አሁን ላይ በሕዝብና ሀገር ላይ የተጋረጡ ፈተናዎችን ለመሻገር የፖለቲካ ልየነቶችን በመተው በአንድነት መሥራት ይገባል ብለዋል።

በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ ላይ የተሳተፉትም  የአረንጓዴ አሻራ ልማት ሀገራዊ ጉዳይ በመሆኑ ነው ያሉት አቶ ፒተር በኮሮና ወረርሽኝም ሆነ በሕዳሴ ግድቡ እየተነሱ ያሉትን ችግሮች ለማለፍ ከሌሎች ጋር በአንድነት እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

ተፎካካሪ ፓርቲዎች በሕዝብና ሀገራዊ ጉዳዩች ዙሪያ በጋራ ለመሥራት በሳዩት ፍላጎት በጋራ የችግኝ ተከላ ማካሄዳቸውን የገለጹት ደግሞ በብልፅግና ፓርቲ የጋምቤላ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ባንቻየሁ ድንገታ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ)  ተወካይ አቶ ጋትላት ጊል በቀጣይ በሌሎች የልማትና ሀገራዊ ጉዳዮች በአንድነት ተባብረው ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተላለፈውን የአረንጓዴ አሻራ ልማት በመደገፍ በመርሃ ግብሩ ላይ መገኘታቸውን ተናገረዋል።

የጋሕፍሰልዴን ተወካይ አቶ ቱል ዴንግ በበኩላቸው ፓርቲያቸው በክልሉ የሚካሄዱ ልማቶች እንደሚደግፍና አብሮ ለመሥራትም ዝግጁ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም