በትግራይ ከ10 ሺህ በላይ ወጣት አርሶ አደሮችን በንብ ማነብ ስራ ለማሰማራት ነው

60

መቐለ፣  ሰኔ 18/2012 (ኢዜአ) በትግራይ ክልል ከ10 ሺህ በላይ ወጣት አርሶ አደሮችን በንብ ማነብ ስራ ለማሰማራት እየተሰራ መሆኑ የትግራይ ክልል ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ ገለጸ።

 በቢሮው የእንስሳት ሃብት ልማት ዳይሬክቶሬት የዓሳና ንብ እርባታ ቡድን መሪ አቶ ጎሹ ወልደአበዝጊ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ የእርሻ መሬት የሌላቸው ወጣት አርሶ አደሮች በመመልመል በንብ ማነብ የስራ ዘርፍ እንዲሰማሩ እየተደረገ ነው ።

በማህበር ለተደራጁ ወጣቶች 16 ቀፎ ንብ በግል ለሚሰሩ ደግሞ ሁለት ቀፎ ንብ እየተሰጣቸው ወደ ስራው እንዲገቡ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

እስከ አሁን ድረስ በግልና በማህበር የተደራጁ 4 ሺህ 500  ወጣት አርሶ አደሮች የንብ አቅርቦት አግኝተው የማነብ ስራ መጀመራቸውን ገልጸዋል።

ቀሪዎቹ ደግሞ እስከ ሐምሌ ባለው ጊዜ ውስጥ ስልጠና ወስደው ወደ ስራ ይገባሉ ተብሏል።

በንብ ማነብ ስራ ለሚሰማሩ ወጣቶች በሞዴል አርሶ አደሮች የተራቡ 80 ሺህ ቀፎ ንብ መዘጋጀቱን አስረድተዋል።

በንብ ማነብ ስራ ለሚሰማሩ ወጣቶቹ  በክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮና በማህበራዊ ረድኤት ትግራይ/ማረት/ የስልጠና፣ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በክልተ አውላዓሎ ወረዳ ቂሀን ቀበሌ ገበሬ አምስት ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው ስራ መጀመራቸውን የገለጸው ደግሞ የማህበሩ አባል ወጣት ሳሙኤል ሐጎስ  ነው።

ወጣቱ እንዳለው በንብ ማነብ ስራ ለመሰማራት ከጠየቁት ግማሽ ሚሊዮን ብር ብድር ውስጥ 250 ሺህ ብር እንደተሰጣቸው ተናግሯል።

ማህበሩ ባገኘው ገንዘብ 20 ቀፎ ንብ በመግዛት በተዘጋጀላቸው ቦታ የማነብ ስራ መጀመራቸውን ጠቅሶ የባለሙያዎች ክትትልና ድጋፍ እንዲደረግላቸው ጠይቋል።

በክልሉ ውስጥ 224 ሺህ አርሶ አደሮች በንብ ማነብ ዘርፍ በመሳተፍ ላይ ሲሆኑ፣ ከመካከላቸው 65 ሺህ ያህሉ የእርሻ መሬት የሌላቸው ወጣቶች ናቸው ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም