በአማራ ክልል በአረንጓዴ አሻራ ቀን በአንድ ጀንበር 205 ሚሊዮን ችግኝ ይተከላል

91

ባሕርዳር፣ ሰኔ18/2012 (ኢዜአ) በአማራ ክልል የአረንጓዴ አሻራ ግብን ለማሳካት በአንድ ጀምበር 205 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል የቦታ ልየታና የጉድጓድ ቁፋሮ ዝግጅት እየተካሄደ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው የተፈጥሮ ሀብት ልማት ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው እንግዳየሁ ለኢዜአ እንደገለጹት የአንድ ጀንበር  የችግኝ ተከላው የሚካሄደው ሐምሌ 6 ቀን 2012 ዓ.ም ነው።

በአንድ ጀምበር በሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም 20 ሺህ 500 ሔክታር የተራቆተ መሬት በተከላው የሚሸፈን መሆኑን ተናግረዋል።

ለችግኝ ተከላ የሚሆነው ጉድጓድም ሙሉ በሙሉ ቁፋሮ መካሄዱን ጠቅሰው ለዚሁ የሚሆን የሀገር ውስጥና የውጭ ዝርያ ያላቸው ችግኞች ተፈልተው ተዘጋጅተዋል።

በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች በሚካሔደው የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ወጣቶችና ኅብረተሰቡ በስፋት ወጥቶ እንዲሳተፍ ከወዲሁ የቅስቀሳና የማደራጀት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል።

ባለፈው ዓመት በዚሁ ተመሣሣይ ፕሮግራም 71 ሚሊዮን ችግኝ በመትከልና እንክብካቤ በማድረግ ከ80 በመቶ በላይ ሊጸድቅ እንደቻለም ተናግረዋል።

ኅብረተሰቡም የኮሮና ቫይረስን በመከላከል ርቀቱን ጠብቆና የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል በመጠቀም የክረምት የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ እንዲያከናውን ይደረጋል።  

በዚህ የክረምት ወቅትም ከአንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን በላይ ችግኝ ተከላ የሚካሄድ ሲሆን እስካሁን በተደረገው እንቅስቃሴም ሁለት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ችግኝ ተተክሏል ብለዋል።

ኅብረተሰቡ የደንን ጥቅምና ጉዳት እየተረዳ መምጣት በየጊዜው የሚተከሉ ችግኞችን በባለቤትነት ስሜት ተንከባክቦ የማሳደግ ልምዱ እያደገ መምጣቱን አስረድተዋል።

በአዊ ዞን አንከሻ ወረዳ የማንጂ ተንኮሻ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ይርጋ ሰሎሞን በሰጡት አስተያየት በዚህ የክረምት ወቅት 2 ሺህ 500 የአካሽያ ዲከረንስና የባሕርዛፍ ችግኞችን ለተከላ ማዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

ከአዘጋጁት ውስጥም አንድ ሺህ የሚሆነውን በራሳቸው መሬት ተክለው ለመንከባከብና ቀሪውን ለሌሎች በመሸጥ ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት እየሰሩ መሆኑን አስረድተዋል።

በዞኑ ፋግታ ለኩማ ወረዳ የእደውኃ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ብርሌው አረጋ በበኩሉ በየዓመቱ በወል መሬት የሚተከሉ ችግኞችን ተደራጅተው እየተንከባከቡ መሆናቸውን  ተናግሯል።

የሚተከሉ ችግኞችን ተንከባክቦ ማሳደግ የአፈር መሸርሸርን እንዲቀንስና የመሬቱ ለምነት እንዲጨምር ጥቅሙ ከፍተኛ በመሆኑ ዘንድሮም መትከል የጀመሩትን ችግኝ ተንከባክቦ ለማሳደግ መዘጋጀቱን አስረድቷል።   

በክልሉ ባለፈው ዓመት የክረምት ወቅት በአረንዴ አሻራና በመደበኛው የችግኝ ተከላ ፕሮግራም 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ችግኝ በመትከል 75 በመቶ መጽደቁን ከቢሮው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም