የደቡብ ክልል መስተዳደር ምክር ቤት በ2ዐ1ዐ በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ላይ ተወያየ

63
ሃዋሳ ሀምሌ 2/2010 የደቡብ ክልል የመስተዳድር ምክር ቤት በክልሉ የአስፈጻሚ ተቋማት የ2ዐ1ዐ በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ላይ መወያየቱን የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡ ጽህፈት ቤቱ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት  በላከው መረጃ እንዳስታወቀው ምክር ቤቱ ከበጀት ዓመቱ ዕቅድ አፈጻጸም ለቀጣይ ሁለት ዓመታት የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትግበራ የሚሆን ልምድና ተሞክሮ ሊወሰድ እንደሚገባ አመልክቷል፡፡ ምክር ቤቱ በአስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች የ2ዐ1ዐ በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማው በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ሥራ ላይ ተደማሪ ለውጥ ቢኖርም ግቡን በተሟላ መልኩ ከማሳካት አንጻር ለቀጣይ የሚተኮርባቸውን ዘርፎች መኖራቸውን ለይቷል፡፡ በእርሻ ዘርፍ በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ማመጣጠን፣ በገበያ ተኮር ሰብሎች ምርታማነት ላይ መረባረብና የአፈር ማዳበሪያን የእጅ በእጅ ሽያጭ እውን ማድረግ አስፈላጊነቱን አስቀምጧል፡፡ በከተማ ልማትና ቤቶች ዘርፍም የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ሥራ ከፋይናንስ እጥረትና ከመስሪያ ቦታ አቅርቦት ችግር ተላቆ የሕብረተሰቡን ፍላጐት በሚያረካ መልኩ እንዲመራም የመስተዳድር ምክር ቤቱ ወስኗል፡፡ የከተሞችና የማዘጋጃ ቤቶች የመልካም አስተዳደር ችግርን መቅረፍ ቁልፍ የትኩረት መስክ መሆን እንዳለበትም ነው ያሳሰበው፡፡ ምክር ቤቱ የንግድ ሥርዓት ሪፎርምና የገቢ ሪፎርም ተጣምረው እንዲፈጸሙ፣ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪውን ዝቅተኛ አፈጻጸም የሚቀይሩ አሠራሮች እና ማበረታቻዎች እንዲተገበሩም አቅጣጫ አስቀምቷል። ከእዚህ በተጨማሪ የመስኖ ዘርፍ ሥራ ከችግር እንዲላቀቅና የክልሉ የመጠጥ ውሃ ሽፋን እንዲያድግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መምከሩን ነው መረጃው ያስታወቅው። በትምህርት ሥራ ላይ የመምህራንን የአቅም ክፍተት እየለዩ በመሙላት በኩልም ውይይት የተደረገ ሲሆን በእዚህም የቴክኒክና ሙያ የስልጠና ጥራትና የኤክስቴንሽን አገልግሎት አሰጣጥ እንዲፈተሽ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ እንደመረጃው ከሆነ፣ በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፍ በዘገባ ሥራ ላይ የሚታየውን የሚዛናዊነትና ወቅታዊነት ችግር እንዲፈታ የባለሙያውን የእውቀትና የክህሎት ክፍተት መሙላት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። በተጨማሪም የግብአት ችግርን በመፍታትና ሚዲያው ነፃነቱን ጠብቆ በኃላፊነት ስሜት እንዲሰራ ማገዝ ተገቢ መሆኑን ምክርቤቱ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ የክልሉን ሕዝቦች ሠላም ማስጠበቅ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር በመሆኑ በጸጥታ ጉዳይ ሰፊ ጊዜ ሰጥቶ በመወያየት ከክልሉ የተፈናቀሉ ዜጐችን የማቋቋም ሥራ በተጀመረው መንገድ እንዲጠናከር አሳስቧል። መስተዳድር ምክር ቤቱ የገቢ ግብርና የታክስ አስተዳደር ደንቦች ላይ ተወያይቶ ያጸደቀ ሲሆን በተሻሻለው የመንግስት ሠራተኞች አዋጅ ላይም ተወያይቶ በመቀበል እንዲጸድቅ ለክልሉ ምክር ቤት እንዲላክ ወስኗል፡፡ የደቡብ ክልል የመስተዳድር ምክር ቤት በ2010 በጀት ዓመትና በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የሁለት ዓመት ተኩል ዕቅድ ትግበራ አፈጻጸሞች ላይ ከተዋያየ በኋላ ምርጥ ተሞክሮዎች እንዲጠናከሩና ጉድለቶች እንዲቀረፉ ወስኗል። የ2011 በጀት ዓመት ዕቅድ በተሟላ መልኩ ተግባራዊ እንዲሆን አቅጣጫ በማስቀመጥ ጉባኤውን ያጠናቀቀው ምክር ቤት በቀጣይ ጥቂት ቀናት ውስጥ በ2ዐ11 በጀት ቀመር ማከፋፈያ ረቂቅ አዋጅ ላይም ይወያያል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የደቡብ ክልል መስተዳደር ምክር ቤት የክልሉ የካቢኔ አባላት በመገናኘት በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች የሚመክሩበት ነው
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም