የጣና ሐይቅን ከሥጋት ለመታደግ ሁለንተናዊ ልማት ያስፈልጋል

75

ባሕርዳር፣ ሰኔ 18/2012 (ኢዜአ) የጣና ሐይቅን ከእምቦጭና ሌሎች ከተደቀኑበት ሥጋቶች ለመታደግ የረጅም ጊዜ ዕቅድ በማውጣት ሁለንተናዊ ልማትና ጥበቃ ያስፈልገዋል ሲሉ ባለድርሻ አካላት ገለጹ።

የአማራ ክልል አካባቢ፣ ደን፣ ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በላይነህ አየለ እንዳሉት የጣና ሐይቅ ችግሩ የእምቦጭ አረም መከሰት ብቻ አይደለም።

ሐይቁ በገባር ወንዞች አማካኝነት በሚገባ ከፍተኛ ደለል የመሞላት፣ የዙሪያው ብዝሃ ሕይወት መጎዳት፣ ብክለትና የሐይቅ ዙሪያ ባሕር ሸሽ እርሻ መስፋፋት ለሐይቁ ደህንነት ሥጋት ናቸው ብለዋል።

በዙሪያው በከፍተኛ ገንዘብ የሚከናወኑ ያልተጠኑ የልማት ፕሮጀክቶችና የውኃ አዘል መሬቶች ለተለያዩ ልማቶች እንዲውሉ መደረጉ ሐይቁ በከፋ ሁኔታ እንዲታመም አድርጎታል።

የእምቦጭ አረም መከሰት የበሽታው ምልክት ነው ያሉት ዶክተር በላይነህ አረሙን ከማጽዳት ባለፈ ወደ ሐይቁ ንጹሕ ውኃ እንዲገባ የሚያግዙ የልማት ሥራዎች መከናወን አለባቸው።

በተለይም በየዓመቱ እየተከናወነ ያለው የአፈርና ውኃ ጥበቃ ሥራዎች ሐይቁን ታሳቢ ተደርጎ ሊከናወን ይግባል ብለዋል።

እምቦጭን በመከላከል ባለፉት ሦስት ዓመታት በተከናወነው ሥራ የሐይቁ ጉዳይ አጀንዳ እንዲሆን መደረጉን ጠቁመው፤ በቀጣይም ሕዝቡን በማስተባበር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።

በሐይቁ ዙሪያ የሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶች የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ የተሠራላቸው መሆን እንዳለበት ጠቅሰዋል።

ለሕዝብ ጠቀሜታ የሚመጡ ፕሮጀክቶች የሐይቁን ጉዳት በመቀነስ መከናወን እንደለባቸው ገልጸው ከዚህ በኋላ የሚመጡ ፕሮጀክቶች ለሐይቁ ሥጋት በማይፈጥር አግባብ መከናወን እንዳለበት አሳስበዋል።

የጣና ሐይቅና ሌሎች የውኃ አካላት ልማትና ጥበቃ ኤጀንሲ ዋና ሥራአስኪያጅ ዶክተር አያሌው ወንዴ በበኩላቸው ሐይቁ በከፋ ቢታመምም መድኃኒቱ ታውቆ እየተሰራ አይደለም ብለዋል።

የሐይቁ በሽታ መገለጫ የሆነው የእምቦጭ አረም መከሰት ቢሆንም ሌሎች ተደራራቢ ችግሮች መከሰታቸውን ገልጸዋል።

እምቦጩን ባለፉት ስምንት ዓመታት በሕዝብ ተሳትፎ ለማስወገድ ቢሞከርም አሁንም ድረስ በ33 ቀበሌዎች ከሁለት ሺህ ሔክታር በላይ የሐይቁ ዳርቻ በአረሙ እንደተወረረ ይገኛል።

የአረሙ መከሰት በአካባቢው ባሉ አርሶ አደሮች ላይ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና ማሳደሩን ጠቅሰው በዓሣ ሀብት፣ በእንስሳት መኖና ብዝሃ ሕይወቱን በማጥፋት ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል።

አረሙ በዓለም ላይ ካሉ እጅግ አደገኛ አረሞች አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ እምቦጩ በሚራባበትና በአደገኛነቱ ልክ ሥራዎች አልተከናወኑም ብለዋል።

በተለይም በችግሩ ልክ የመግባባትና ተቀናጅቶ የመሥራት ሰፊ ክፍተት መኖሩን አመልክተው ይህም መፍትሔውን ሩቅ አድርጎታል ብለዋል።

ሐይቁ የሀገር ሀብት በመሆኑና የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዋና የውኃ ምንጭ በመሆኑ ከሥጋት ለመታደግ የረጅም ጊዜ ስትራቴጂክ ዕቅድ በማውጣት በተቀናጀ አግባብ መሥራት እንደሚገባም አብራርተዋል።

በሐይቁ ዙሪያ የሚገኙ አርሶ አደሮች በእንስሳት እርባታ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በሌሎች የሐይቁን ጫና በሚቀንሱ የገቢ ማስገኛ ሥራዎች ማሰማራት እንደሚገባም ገልጸዋል።

በሐይቁ ዙሪያ እየተሰሩ ያሉ ተግባራት ሁሉ ሐይቁን በጊዜያዊነት የሚታደጉ ናቸው ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ማማሩ አያሌው ናቸው።

ሐይቁ የገዘፈ ችግር ያለበት ቢሆንም በቅንጅት መጓደልና በትኩረት ማነስ በሚገባው ልክ ሥራዎች  አየተከናወኑ አይደለም ብለዋል።

የእምቦጭ አረሙ በፍጥነት ከመራባት ባህሪው አንፃር ሲመዘን በመደበኛ ሥራ ብቻ ማስወገድ እንደማይቻልም ተናግረዋል።

የጣና ሐይቅን ከሥጋት የመታደግ ሥራው የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ጭምር መታደግ በመሆኑ የእዚያው አካል ሆኖ መሥራት አለበት ሲሉ ገልጸዋል።

አሁን ላይ የእምቦጭ አረም ጢስ ዓባይ ደርሷል ያሉት ዶክተር ማማሩ በዚህ ክረምት ሕዳሴ ግድብ የማይደርስበት ምንም ምክንያት እንደሌለ አመልክተዋል።

የፌደራል መንግሥት ከክልሉ መንግሥት ጋር በመደጋገፍ በቴክኖሎጂ፣ በሰው ኃይልና ሌሎች ዘዴዎችን በመተግበር ሐይቁ ከማይመለስበት ደረጃ ከመድረሱ በፊት መታደግ እንደሚገባ አብራርተዋል።

የእምቦጭ አረም 2003 ዓ.ም የተከሰተ ሲሆን ባለፉት ዓመታት የመከላከል ሥራ ሲከናወን ቆይቷል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እምቦጭን ለመከላከል እስከ 300 ሚሊዮን ብር ወጭ እንደሚደረግ መግለጻቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም