ሚኒስቴሩ በሚያካሂዳቸው ሜጋ ፕሮጀክቶችና በሌሎችም የልማት ስራዎች 63 ሺህ ለሚጠጉ ዜጎች የሥራ እድል ተፈጥሯል

70
አዳማ ሀምሌ  2/2010 የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር በሚያካሂዳቸው ሜጋ ፕሮጀክቶችና ሌሎች የልማት ስራዎች 63 ሺህ ለሚጠጉ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠሩን አስታወቀ። በሚኒስቴሩ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ሜይንስትሪሚንግ  ዩኒት አስተባባሪ አቶ አስፋው ገብረወልድ እንዳስታወቁት በዚህ ዓመት በገጠር የሥራ ዕድል ኘሮግራም ከተፈጠረባቸው መስኮች መካከል የውሃና ሳኒቴሽን፣ መስኖና ድሬኔጅ የልማት ፕሮጀክቶች ይገኙበታል። በተፋሰስ ልማት፣ በኤሌክትሪክ ኃይልና አገልግሎት እንዲሁም በአማራጭ ኢነርጂ ልማት ዘርፍ  በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት ለተደራጁም የስራ እድሉ ተመቻችቷል። ''በተለይ በተፋሰስ እንክብካቤና ልማት ስራዎች የስራ እድል ከተፈጠረባቸው አከባቢዎች መካከል የዝዋይ፣ ሻላ፣ የአባያ ጫሞና ቀይ ባህር የተፋሰስ ልማት ፕሮጀክት፣ መልካ ዋከና የተቀናጀ ልማትና እንክብካቤ ፕሮጀክት፣ ጊቤ ተፋሰስ ፕሮጀክት ይገኙበታል'' ብለዋል። በእነዚህና በሌሎችም የተፋሰስ እንክብካቤና ልማት ሥራዎች በሚካሄዱባቸው ፕሮጀክቶች አካባቢ ለሚገኙ 22 ሺህ 296 ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ጠቅሰዋል። አርጆ ዲዴሳ፣ መገጭ፣ ዛሪማ፣ ጊዳቦ፣ የርብና ኢትዮ ናይል የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶችም ለ10 ሺህ 765 ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡ መልካሰዲ፣ ገናሌ ዳዋና ጊቤ 3፣ አሎቶ ጂኦተርማል፣ አባ ሳሙኤልና በሌሎችም ኃይል ማመንጫና ኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ ፕሮጀክቶች አካባቢ ያሉ ዜጎችም የሥራ ዕድሉ ተጠቃሚ ሆነዋል። በሁሉም ክልሎች 137 የመስመር ግንባታ ኢንተርፕራይዞች እና 120 በኮንክሪት ፖል ምርት የተሰማሩ ኢንተርፕራይዞችም የስራ እድሉ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መደበኛ ሥራዎችም ለ13 ሺህ 876 ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን ነው  አቶ አስፋው ያብራሩት። ሚኒስቴሩ በውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ዘርፍ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ያሉ ጸጋዎች፣ ግኝቶችና ያጋጠሙ ተግዳራቶች ዙሪያ ጥናት በማካሄድ ያገኘውን ግብአት በመጠቀም በአዲሱ የበጀት ዓመት ለገጠር ስራ እድል ፈጠራ ፕሮግራም ስኬታማነት የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል። በግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴር የገጠር ሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ መንግስቴ በበኩላቸው በ2017 ዓ.ም መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ ለመሰለፍ በሚደረገው እንቅስቃሴ እንደማነቆ ከተቀመጡት ተግዳሮት አንዱ የስራ አጥነት ችግር ነው። ችግሩን ለማቃለል የገጠር ሥራ ዕድል ፈጠራ ፕሮግራም ተነድፎ ካለፈው ዓመት ወዲህ ለተግባራዊነቱ ሁሉም ክልሎች በባለቤትነት ወደ ስራ እንዲገቡ ተደርጓል ብለዋል። በ2010 በጀት ዓመት በግብርናና ከግብርና ውጪ ባሉ ዘርፎች ከአንድ ሚሊዮን ለሚበልጡ ወጣቶች የስራ አድል ለመፍጠር ታቅዶ ለአንድ ሚሊዮን 575 ሺህ 638 ዜጎች የስራ እድል መፍጠር መቻሉን ጠቅሰዋል። በቀጣይም እስከ 2ኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የትግበራ ዘመን መጨረሻ ድረስ 4 ነጥብ 7 ሚሊዮን ስራ ፈላጊዎችን በገጠር ተጠቃሚ ለማድረግ የተያዘውን ግብ ለማሳካት ርብርብ እንደሚደረግ ሚኒስትር ዴኤታው አስታውቀዋል። በገጠር የስራ እድል ፈጠራ ረገድ የተከናወነውን ስራ ለማስተዋወቅና ውጤታማ የሆኑ ኢንተርፕራይዞችን ለማበረታታት  በሚኒስቴሩ አዘጋጅነት “አንደኛው ዙር ሃገር አቀፍ የገጠር ስራ ዕድል ፈጠራ ኤግዚቢሽንና ባዛር” በቅርቡ በአዳማ ከተማ መካሄዱ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም