የዓለም ከ20 ዓመት በታች የወጣቶች አትሌቲክስ ውድድር ነገ በፊንላንድ ይጀመራል

110
አዲስ አበባ ሓምሌ 2/2010 የዓለም ከ20 ዓመት በታች የወጣቶች አትሌቲክስ ውድድር ነገ በፊንላንድ ቴምፔሬ ከተማ ይጀመራል። በውድድሩ መክፈቻ ላይ ኢትዮጵያዊያን የሚሳተፉበት የ10 ሺህ ሜትር ወንዶችና የ5 ሺህ ሜትር ሴቶች ፍጻሜ ውድድሮች ይካሄዳሉ። ነገ ምሽት 12 ሰአት ከ50 ደቂቃ ላይ በሚካሄደው የ10 ሺህ ሜትር ወንዶች የፍጻሜ ውድድር በሪሁ አረጋዊና ኦሊቃ አዱኛ ይሳተፋሉ። ከማራቶን ውድድሮች ወደ ረጅም ርቀት የመም ላይ ውድድሮች ትኩረቱን ያደረገው አትሌት በሪሁ በግንቦት ወር 2010 ዓ.ም በአሰላ ከተማ በተካሄደው ስድስተኛው የኢትዮጵያ ወጣቶች አትሌቲክስ ውድድር በ10 ሺህ ሜትር አሸናፊ መሆኑ ይታወሳል። አትሌቱ በአሰላው ውድድር 29 ደቂቃ ከ36 ሴኮንድ ከ97 ማይክሮ ሴኮንድ በመግባት በርቀቱ የግሉን ምርጥ ሰዓት አስመዘግቧል። በአሰላው ውድድር በ10 ሺህ ሜትር ሁለተኛ የወጣው ኦሊቃ አዱኛ በነገው የ10 ሺህ ሜትር ውድድር የሚሳተፍ ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ነው። አትሌት ኦሊቃ በአሰላው ውድድር 29 ደቂቃ ከ37 ሴኮንድ ከ12 ማይክሮ ሴኮንድ በሆነ ጊዜ ያጠናቀቀ ሲሆን ይህም በርቀቱ የግል ምርጥ ሰአቱ ሆኖ ተመዝግቦለታል። ከቀኑ 11 ሰአት ከ40 ደቂቃ ላይ በሚካሄደው የ5 ሺህ ሜትር ሴቶች ውድድር ደግሞ አትሌት ግርማዊት ገብረእግዚአብሔርና አትሌት እጅጋየሁ ታዬ ይሳተፋሉ። አትሌት ግርማዊት በመካከለኛና በረጅም ርቀት የመም ውድድሮች በተጨማሪ በአገር አቋራጭ ውድድሮች ላይ ጥሩ የሚባል ተሳትፎና ውጤት አላት። አትሌቷ በግንቦት ወር 2010 ዓ.ም በኦሮሚያ አሰላ ከተማ በተካሄደው ስድስተኛው የኢትዮጵያ ወጣቶች አትሌቲክስ ውድድር በ5 ሺህ ሜትር ውድድር 15 ደቂቃ 48 ሴኮንድ 81 ማይክሮ ሴኮንድ የገባችበት ጊዜ የርቀቱ የግል ምርጥ ሰአቷ ነው። ሌላኛዋ ተወዳዳሪ አትሌት እጅጋየሁ ታዬ በአሰላው ወድድር ግርማዊትን ተከትላ ሁለተኛ መውጣቷ የሚታወስ ሲሆን በመጋቢት ወር 2010 ዓ.ም በአልጄሪያ ክሌፍ በተካሄደው 5ኛው የአፍሪካ አገር አቋራጭ ውድድር በ6 ኪሎ ሜትር ወጣት ሴቶች ውድድር ስድስተኛ ወጥታለች። ከሁለቱ ፍጻሜ ውድድሮች በተጨማሪ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች የሚሳተፉባቸው የማጣሪያ ውድድሮች ይካሄዳሉ። በነገው እለት ከረፋዱ 4 ሰአት ከ5 ደቂቃ በሚካሄደው የ1 ሺህ 500 ሜትር ወንዶች  አትሌት ሳሙኤል ተፈራና አትሌት ብርሃኑ ሶሬሳ ከረፋዱ 4 ሰአት ከ40 ደቂቃ በ800 ሜትር ሴቶች አትሌት ደርቤ ወልተጂ እና ፍሬወይኒ ሃይሉ ይሳተፋሉ። ከቀኑ 10 ሰአት ከ50 ደቂቃ በ400 ሜትር ሴቶች በሚካሄደው ማጣሪያ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ፍሬህይወት ወንዴና ማህሌት ፍቅር ይወዳደራሉ። ኢትዮጵያ በፊንላንድ በሚካሄደው ውድድር 29 አትሌቶችን ይዛ ከ400 ሜትር ጀምሮ እስከ 10 ሺህ ሜትር ባሉ ርቀቶችና በእርምጃ እና በመሰናክል ውድድሮች ትካፈላለች። ከትናንት በስቲያ ፊንላንድ የደረሱት የኢትዮጵያ አትሌቶች የመጀመሪያ ልምምድ እዛው ማድረጋቸውን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። በውድድሩ ላይ ከ158  አገራት የተውጣጡ 1 ሺህ 462  አትሌቶች በተለያዩ ርቀቶች እንደሚካፈሉ የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ገልጿል። የዓለም ከ20 ዓመት በታች የወጣቶች አትሌቲክስ ውድድር እስከ ሐምሌ 8 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ ይካሄዳል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም