በጉጂና በምስራቅ ወለጋ ዞኖች የልማት ፕሮጀክቶች ተመረቁ

65

ነገሌ/ነቀምቴ/ ሰኔ 17/2012 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል በጉጂና በምስራቅ ወለጋ ዞኖች የተገነቡ የልማት ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ዝግጁ መሆናቸውን የየአካባቢው የስራ ኃላፊዎች ገለፁ ። 

በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን በ55 ሚሊዮን ብር ወጭ የተገነቡ ፕሮጀክቶች ተመርቀው ከትናንት ጀምሮ ለአገልግሎት ክፍት መሆናቸውን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደለ  ኡዱ ገልፀዋል፡፡

በክልሉ ግንባታቸው ተጀምረው ለአመታት የተጓተቱ የመሰረተ ልማት ስራዎች የመልካም አስተዳደር ችግር ሆነው መቆየታቸውን አስታውሰው የለውጥ ሀይሉ ባደረገው ርብርብ፣ ድጋፍና ክትትል የአብዛኛዎቹ ፕሮጀክቶች የግንባታ ስራ መጠናቁን ጠቁመዋል፡፡

ደረጃ በደረጃ በመንግስት እየተፈታ ያለው የመሰረተ ልማት ግንባታና የመልካም አስተዳደር ችግር በተግባር መሬት እንዲይዝ የተጠቃሚው ህዝብ ድጋፍና ትብብር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በዞኑ ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት የሆኑት ፕሮጀክቶች የአዶላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና የቦሬ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ መንደር እንደሆኑ አብራርተዋል፡፡

ትምህርት ቤቱ 1 ሺህ 200 ተማሪዎችን የመቀበል አቅም ሲኖረው የአትሌቲክስ መንደሩ ደግሞ 250 ወጣት አትሌቶችን ተቀብሎ ማሰልጠን ይችላል ።

ለፕሮጀክቶቹ ግንባታ የዋለው 55 ሚሊዮን ብር ሙሉ በሙሉ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የተመደበ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡

የአዶላ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ ጡሩነሽ ቦሩ በመንግስት የተጀመረው የመሰረተ ልማትና የመልካም አስተዳደር ችግር አፈታት ቀጣይነት እንዲኖረው ጠይቀዋል፡፡

የዚሁ ወረዳ ነዋሪ አቶ ዋቆ ሞሉ በበኩላቸው በሰላም ፣ በልማትና በመልካም አስተዳደር ላይ ያሉ ችግሮች እንዲፈቱ የፌደራልና የክልሉ መንግስት ከዞኑ ህዝብ ጋር በትብብር ቢሰሩ መልካም ነው የሚል አስተያየት ሰጥተዋል ።

በሌላ በኩል ደግሞ በምሥራቅ ወለጋ ዞን የሲቡ ስሬን እና የዋማ አገሎ ወረዳዎችን የሚያገናኝ ድልድይ በ14ነጥብ 5  ሚሊዮን ብር ተገንብቶ በትናንትናው ዕለት ተመርቋል ።

የሲቡ ስሬ ወረዳ መንገዶች ባለሥልጣን ሃላፊ አቶ ገመዳ ያደታ እንደገለፁት  ሁለቱን ወረዳዎች የሚያገናኝና በለገ ቶራ ወንዝ ላይ የተገነባው ድልድይ 20 ሜትር ርዝመትና 7 ሜትር ስፋት አለው ።

ድልድዩ በክረምት ወቅት ሲያጋጥማቸው ለቆየው ችግር መፍትሄ የሰጠ መሆኑን እንዳንድ የአከባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል ።

የጃርሶ ዋማ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ምትኩ ገመቹ በሰጡት አስተያየት ወንዙ ላይ መሻገሪያ ድልድይ ባለመኖሩ በክረምት ወራት በሰውና በእንስሳት ህይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሲያደርስ እንደነበር
ገልጸዋል ።

ድልድዩ ተገንብቶ ለአገልግሎት በመብቃቱ መደሰታቸውን ገልጸው፣ የግብርና ምርታቸውን ያለ ስጋት  ወደ ገበያ ወስደው በተሻለ ዋጋ ለመሸጥ እንደሚያስችላቸው አስረድተዋል ።

ሌላው የቀበሌው ነዋሪ አርሶ አደር ጫሊ እንኮሳ በበኩላቸው የግብርና ምርታቸውን ወደ ገበያ በሚያጓጉዙበት ወቅት እንስሳትን ከነጭነታቸው በጎርፍ በመውሰድ ለችግር ሲዳርጉ እንደነበር ገልፀዋል ።

አሁን የድልድዩ ግንባታ ለችግራቸው ዘላቂ መፍትሔ ይሆናል የሚል እምነት እንዳላቸው አርሶ አደሩ ተናግረዋል ።

በክልሉ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ በአቶ ፍቃዱ ተሰማ የተመራው የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ከድልድዩ ምረቃ በኋላ በዋዩ ቱቃ ወረዳ በቦነያ ሞሎ ቀበሌ በክላስተር የተዘራውን የበቆሎ እርሻ እና በሲሬ ከተማ በ72 ሚሊዮን ብር እየተገነባ ያለውን የንጹህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ጎብኝቷል።

የክልሉ መንግሥት የህዝቡን የመሰረተ ልማት ፍላጎት በየደረጃው ተደራሽ በማድረግ በተለይ አርሶ አደሩን ወደ እርሻ ሜካና ይዜሽን ለማሸጋገር እየሰራ መሆኑን አቶ ፍቃዱ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም