ለድሬዳዋና ሲቲ ዞን የሚያገለግል አዲስ የኮቪድ 19 ህክምና ማዕከል ሥራ ጀመረ

121

ድሬዳዋ ሰኔ 17/2012 (ኢዜአ) ለድሬዳዋና ለሶማሌ ክልል ሲቲ ዞን የሚያገለግል አዲስ የኮቪድ 19 ህክምና ማዕከል ሥራ መጀመሩን የሀገር አቀፍ ኮሮና ድጋፍ ሰጪ ግብረ-ኃይል አስታወቀ። 

በግብረ-ኃይል የክልሎች  ድጋፍ አስተባባሪ ዶክተር ፅጌረዳ ክፍሌ  እንደገለጹት ስራ ትናንት የጀመረው ማዕከሉ በተለይ ከጅቡቲ ወደ ሀገራቸው ለሚገቡ ዜጎች የተሻለ ድጋፍ ለማድረግ የተመቻቸ ነው፡፡

የህክምና ማዕከሉ ባሙያዎችና ግብአቶች ተሟልተውለታል ብለዋል፡፡

ማዕከሉን የሚከታተል  የፌደራል መንግስት  ያለበት  አብይና የቴክኒክ ኮሚቴ መዋቀሩን አመልክተው በድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል  ከንቲባ  የሚመራው መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ደወሌ የማቆያ ጣቢያ የነበሩና በቫይረሱ የተገመቱ ሰዎች ወደ  ህክምና ማዕከሉ  ገብተው የተሻለ  ድጋፍ  እንዲያገኙ ለማስቻል  ስራ  መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡

የደወሌው ለአያያዝ አመቺ ባለመሆኑ  መንግስት እንዲዘጋ መወሰኑንና  በስፍራው የሚገኙ ከጅቡቲ ተመላሾች ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ  በተዘጋጀው ማቆያ  ጣቢያ መግባት መጀመራቸውን  ዶክተር ጽጌረዳ አስረድተዋል፡፡

"እነዚህ ዜጎች ከሳምንት ቆይታ በኋላ ተመርምረው ነጻ የሆኑት ወደ የቤታቸው ይመለሳሉ፤ቫይረሱ የተገኘባቸው  ደግሞ ወደ አዲሱ የህክምና  ማዕከል እንዲገቡ ይደረጋል" ብለዋል፡፡

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ አስተዳደር ንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት  ቢሮ ኃላፊና የማዕከሉ አስተባባሪ አቶ ከድር ጁሃር  በበኩላቸው ማዕከሉ ለ750  ሰዎች አገልግሎት መስጠት እንደሚችል  ገልፀዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት  በድሬዳዋ የቫይረሱ ስርጭት እየጨመረ በመምጣቱ አስተዳደሩ ችግሩን ለመቆጣጠር ሲባል የተወሰኑ አካባቢዎችን እንቅስቃሴ ሊገድብ ይችላል ብለዋል፡፡

የሚገደቡት  አካባቢዎች የመለየት ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም  ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ ቸልተኝነት በመተው የሚተላለፉለትን የመከላከያ መመሪያዎች በአግባቡ እንዲተገብርም   አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም