ሚኒስቴሩ በሀገሪቱ ከተሞች አንድ ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል እንቅስቀሴ ጀመረ

64

ገላን፣ ሰኔ 16/2012 (ኢዜአ) የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በሀገሪቱ ከተሞች አንድ ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል እንቅስቃሴ ጀመረ።

እንቅስቀሴው የተጀመረው ዛሬ በገላን ከተማ ከሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማት ሥር ከተደራጁ ልህቀት የወጣቶች ኅብረት በተባለው ባለሙያ ወጣቶች ጋር ነው።


ዛሬ በይፋ በተጀመረው የልህቀት የወጣቶች ኅብረት የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም በገላንና ቢሾፍቱ ከተሞች አምስት ሺህ ችግኝ ተተክሏል።

ከሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማቱ የተውጣጡት ወጣት ባለሙያዎቹ ከችግኝ ተከላ በተጨማሪ የአቅም ግንባታ ሥራዎችና ሌሎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ከሚያከናውኗቸው መካከል እንደሚገኙባቸው የወጣቶቹ አስተባባሪ ታዬ ሣሙኤል ተናግሯል።

ከመደበኛ የቢሮ ሥራ በተጨማሪ ያላቸው ሙያና የወጣትነት አቅማቸውን በተግባር ማዋልና ሀገሪቷን የሚጠቅሙ ሥራዎችን ማከናወን የኅብረቱ ዓላማ ነው።

በተለይም ሌሎች ወጣት ባለሙያዎችም በሚችሉት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ እንዲሰማሩም ወጣት ታዬ መልዕክቱን አስተላልፏል።

የሚተከሉት ችግኞች ጸድቀውና አድገው ለማየት ኅብረተሰቡ ከኮሮና ራሱን በመጠበቅ በአረንጓዴ አሻራው በንቃት መሳተፍ እንዳለበት የተናገረችው ደግሞ የኅብረቱ መሥራችና አባል ወጣት ሃይማኖት ጥላሁን ናት።

በችግኝ ተከላ መርሃ ግብሩ የተገኙት የሚኒስቴሩ ተወካይ አቶ ጀሚል ኑረዲን እንደገለጹት መሥሪያ ቤታቸው በሥሩ በተደራጁት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጪ ወጣቶቹ ከሚሰሯቸው ተግባራት መካከል ዋነኛው ምቹና አረንጓዴ ከተሞችን መፍጠር ነው።

ለዚህ ሥራ ደግሞ ወጣት ባለሙያዎቹ ውድ የሆነውን ደም በመስጠት በጀመሩት ልዩልዩ ተግባራት በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም ብቻ በሀገሪቱ ከተሞች አንድ ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል አቅዶ ወደ ሥራ መግባታቸውን አስታውቀዋል።

በዚህ ተግባርም ከተሞች ቦታ፣ ችግኝ በማሰናዳትና ከሚኒሰቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር በመትከል የመርሃ ግብሩ አካል እንዲሆኑም ጥሪ አቅርበዋል።

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ዛሬ በጀመረው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በገላን ከተተከለው ሦስት ሺህ ችግኝ በተጨማሪ በቢሾፍቱም ከሁለት ሺህ በላይ ችግኝን ተክሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም