ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከተመድ ዋና ፀሃፊ አንቶንዮ ጉተሬዝ ጋር ይወያያሉ

100
ሐምሌ 2/2010 የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከኤርትራው የሰላም ስምምነት መልስ ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ከተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሀፊ አንቶንዮ ጉተሬዝ ጋር ወያያሉ፡፡ ሮይተርስ አዲስ አበባ የሚገኙ ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው  ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ  በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ለሁለት አስርት ዐመታት  ነግሶ የቆየውን አለመግባባት ለመቋጨት ትናንት ከኤርትራው ፕሬዝዳንት ጋር የደረሱትን ስምምነት ተከትሎ ነው ውይይቱ ካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው፡፡ ትናንት በኤርትራ ዋና ከተማ አስመራ ጉብኝት ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና በአስመራ ነዋሪዎች ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡ በጉብኝታቸውም ሁለቱ ሀገራት ኢኮኖሚያዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለመጀመር አዲስ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ የኤርትራው ፕሬዝዳንት ትናንት ምሽት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ለሚመራው ልዑክ በቤተ መንግሥታቸው የእራት ግብዣ ፕሮግራም አዘጋጅተዋል፡፡ በፕሮግራሙ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ይፋ እንዳደረጉት የሁለቱ ሀገራት አየር መንገዶችና የኤርትራ ወደቦች ስራ እንዲጀምሩና የሁለቱ ሀገራት ህዝቦች በነጻነት ተንቀሳቅሰው እንዲጠያየቁ ተስማምተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም