ሃገር አቀፍ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጀመረ

127

ደብረ ብርሃን፣  ሰኔ16/2012 (ኢዜአ) በሃገሪቱ 10 ነጥብ አንድ ሚሊዮን ወጣቶችን ተሳታፊ የሚያደርገው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በደብረ ብርሃን ከተማ ዛሬ መጀመሩን የፌደራል ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር አስታወቀ።

የ2012/13 ሃገር አቀፍ ክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በደብረ ብርሃን አትሌቲክስ መንደር ማሰልጠኛ ማዕከል በችግኝ ተከላ ተጀምሯል።

በሚኒስቴሩ የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ህይዎት ሃይሉ እንደገለፁት በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ወጣቶች የሚሳተፉበት 10 የስራ ዘርፎች ተለይተዋል።

በተለይ በዚህ የክረምት ወቅት በአካባቢ ጥበቃ ስራ በመሳተፍ የታላቁን የህዳሴ ግድብ ከደለል ለመታደግና የጣናን እምቦጭ በመንቀል ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል።

እንዲሁም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽን ለመከላከል በበጋው ወቅት የተጀመሩ ስራዎች የበለጠ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።

ሌሎች የማህበራዊ አገልግሎት፣ የደን ልማት፣ ደም ልገሳ፣ የእርሻ ስራና መሰል ተግባራት በተቀናጀ አግባብ የሚቀጥሉ መሆናቸውን አብራርተዋል።

በወጣቶቹ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎትም 23 ሚሊዮን ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት እንደሚከናወኑ አስታውቀዋል።

ኮቪድ-19 ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮም ሁለት ሚሊዮን ወጣቶችን በመሳተፍ ለ49 ሚሊዮን ዜጎች ትምህርት በመስጠት፣ እጅ በማስታጠብ፣ ማዕድ በማጋራት ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

የክረምት ወቅት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ስኬታማ እንዲሆንም በየደረጃው ያለው አመራር ተገቢውን ድጋፍና ክትትል እንዲያደርግም ሚኒስቴር ድኤታዋ አሳስበዋል።

የአማራ ክልል ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ አባይነህ መላኩ በበኩላቸው አራት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ወጣቶችን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በማሳተፍ የተለያዩ የልማት ስራዎች ይከናወናል።

በዚህም የክረምት ወቅትም የእንቦጭ አረም በማረምና፣ የኮሮና ወረርሽን በመከላከልና አረጋውያንን በመደገፍ ትኩረት ይደረጋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገብረፃዲቅ በበኩላቸው ባለፈው የበጋ ወራት ወጣቱ በደም ልገሳ በመሳተፍ 600 ዩኒት ደም በአንድ ቀን መሰብሰብ ተችሏል።

በዚህ የክረምት ወቅት 267 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል የታቀደ ሲሆን ወጣቶች በንቃት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

የዚህ ክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት "በጎነት ለአብሮነት በሚል መሪ ሃሳብ" የተጀመረ ሲሆን በስነ ስርዓቱም የፌደራል፣ የክልልና የዞን አመራሮች ተገኝተዋል

 ከሰዓትም ፓናል ውይይት እንደሚካሄድ ከወጣው ፕሮግራም ለማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም