በሶስትዮሽ ድርድሩ እየተንጸባረቀ ያለው አቋም የኢትዮጵያን በዓባይ ወንዝ የመጠቀም መብት ለማሳጣት የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው

70

አዲስ አበባ ሰኔ 15/2012 (ኢዜአ) በሶስትዮሽ ድርድሩ እየተንጸባረቀ ያለው አቋም የኢትዮጵያን በዓባይ ወንዝ የመጠቀም መብት ለማሳጣት የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው ሲሉ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተደራዳሪ ቡድን አባላት አስታወቁ።

በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አዘጋጅነት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁኔታ ላይ የጋራ ግንዛቤ መያዝና አገራዊ ንቅናቄ መፍጠርን ዓላማ ያደረገ የምሁራን የዌቢናር ውይይት ዛሬ ተካሄዷል።

ውይይቱ "ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የህልውናችን ፕሮጀክት" በሚል መሪ ሀሳብ ነው የተካሄደው።

በአገር ውስጥና በውጭ አገራት የሚኖሩ ምሁራን በርዕሰ ጉዳዩ ላይ የመነሻ ፅሁፍ አቅርበው ውይይት ተካሂዶበታል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተደራዳሪ ቡድን አባል ዶክተር ይልማ ስለሺ የግድቡ ፕሮጀክት ዓላማ ኢትዮጵያ የማንንም ጥቅም ሳትጎዳ በተፈጥሮ ሀብቷ ተጠቅማ ኤሌክትሪክ ማመንጨትና መልማት እንደሆነ ገልጸዋል።

እንደ እርሳቸው ገለፃ የቅኝ ግዛት ስምምነቶቹ ሲፈረሙ፣ ሱዳንና ግብጽ የተለያዩ ግድቦችን ሲገነቡና ሲለሙ ኢትዮጵያን አላስፈቀዱም፤ አላማከሩም።

ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን መገንባት ከጀመረች ጀምሮ ግን ሁለቱ አገራት ግድቡ ሊፈርስ ይችላል፣ የግድቡ ደህንነት ቢታይ፣ የምናገኘው የውሃ መጠን ሊቀንስ ይችላል፣ የውሃ አሞላሉ ጉዳት ሊያደርስብን ይችላል የሚሉ ሃሳቦችን ሲያነሱ ቆይተዋል።

በመጨረሻ ደግሞ ኢትዮጵያ ሌሎች አገራትን ሳታማክር ነው ግድቡን እየሰራች ያለችው የሚል ሀሳብ ይዘው መምጣታቸውን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያም ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት በትብብር መንፈስ ስለ ግድቡ ስታስረዳ መቆየቷንና በዚህም ላይ አገራቱ መግባባት ላይ መድረሳቸውን ጠቅሰዋል።

ግብጽና ሱዳን የዓባይን ወንዝ መሰረት በማድረግ ግድቦችና ፕሮጀክቶችን ሲሰሩ ኢትዮጵያን አማክረዋል ወይ? ሲሉ ጥያቄ አዘል ሀሳብ ያነሱት ዶክተር ይልማ ያለ ኢትዮጵያ ይሁንታ ብዙ መስራታቸውን ጠቁመዋል።

በሶስትዮሸ ድርድሩ ያለው ጥያቄ ግድቡ ሳይሆን ከእሱ አልፎ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ የመጠቀም መብቷን እንድታጣ የማድረግ እንቅስቃሴ ነው ብለዋል።

ሁለቱ አገራት የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌትን የድርድር ሂደት እንደ መያዣ ተጠቅመው እኛ ሳንፈቅድ ዓባይ ወንዝን አትጠቀሙም የሚል አቋም እንዳላቸውም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ግድቡን ውሃ ለመሙላትም ሆነ በዓባይ ወንዝ ለመጠቀም የማንም ይሁንታ እንደማያስፈልጋት ነው ያስረዱት።

ሌላው የህዳሴ ግድብ ተደራዳሪ ቡድን አባል አምባሳደር ኢብራሂም እድሪስ በበኩላቸው ግብፅ በድርድሩ ላይ ያቀረበችው የህግ ማዕቀፍ ሀሳብ ኢትዮጵያን በግድቡና በዓባይ ወንዝ እንዳትጠቀም ማሰርን ዓላማ ያደረገ ነው ብለዋል።

ለኢትዮጵያዊያን አሁን ትልቁ መፍትሔ ግድቡን ገንብቶ መጨረስ እንደሆነና ለዚህም ሁሉም በአንድነት ሊቆም እንደሚገባ አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ ግድቡን ውሃ እንዳትሞላ የሚያደርግ ምንም አይነት የህግ ማዕቀፍ ስለሌለ እ.አ.አ በ2015 በሱዳን ካርቱም በተፈረመው የመርሆዎች ስምምነት መሰረት የውሃ ሙሌቷን ታከናውናለች ብለዋል።

ከአሜሪካ የውይይት መነሻ ሀሳብ ያቀረቡት የኢኮኖሚ ባለሙያ ዶክተር ዮናስ ብሩም ኢትዮጵያ በድርድሩ ያሳየችው አቋም ጠንካራና ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው እንደሆነ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድቡና በዓባይ ወንዝ ያላትን አቋም ይበልጥ ለማንጸባረቅ ዓለም አቀፍ የህዝብ ግንኙነት ላይ በትኩረት መስራት እንዳለባት ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ የዓባይን ወንዝ በተመለከተ የተደራጀ የመረጃ ቋት ሊኖራት እንደሚገባ ገልጸው ይህም ለጥናትና ምርምር እንዲሁም በተቀናጀ መረጃ ተጽዕኖ ለመፍጠር እንደሚያስችል አክለዋል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ ውይይቱ በዕውቀት ላይ የተመሰረተና ቁልፍ ሀሳቦች የተነሱበት እንደሆነ ተናግረዋል።

ሚኒስቴሩ በቅርቡ በህዳሴ ግድብና በዓባይ ወንዝ ላይ ጥናትና ምርምር የሚያደርግ የምሁራን ጥምረት እንደሚመሰርትና ውሃ ላይ ጥናትና ምርምር የሚያደርጉ ተቋማትን እንደሚያደራጅ ነው የገለጹት።

የትምህርትና የሳይንስ ማኅበረሰብ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና ሌሎች ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ለሚመሩ ፕሮጀክቶች የማያቋርጥ ድጋፉን ያደርጋል ብለዋል።

የትምህርትና የሳይንስ ማኅበረሰቡ ግድቡን አስመልክቶ ባለ ዘጠኝ ነጥብ የአቋም መግለጫ ያወጣ ሲሆን  በእውቀትና በገንዘብ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግና ግድቡ እውን እንዲሆን ያላሰለሰ ጥረት እንደሚያደርግም ገልጿል።

የዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች፣ የውሃ ጥናትና ምርምር፣ ዓለም አቀፍ ስምምነትና ግድቦች ግንባታ መስኮች ላይ የሚሰሩ ምሁራንና ሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በውይይቱ ተሳትፈዋል።

በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የውይይት መድረክ ሲካሄድ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን ከሶስት ወር በፊት ተመሳሳይ ውይይት ማዘጋጀቱም ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም