ለዓመታት አገልግሎት ሳይሰጡ የቆዩ ሼዶች በ300 ሚሊዮን ብር የማሻሻያ ስራ በማካሔድ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ተደረገ

38

ሀዋሳ፣ ሰኔ 15/2012 ዓ.ም (ኢዜአ)  በደቡብ ክልል በተለያዩ ከተሞች ተገንብተው ለበርካታ ዓመታት አገልግሎት ሳይሰጡ የቆዩ የማምረቻ ሼዶችን ከ300 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የማሻሻያ ሥራ በማካሔድ ጥቅም ላይ እንዲውሉ መደረጉን የክልሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ገለፀ።

የኮርፖሬሽኑ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ናትናኤል ሚሊዮን እንደገለፁት በክልሉ ንግድና ኢዱስትሪ ልማት ቢሮ በተመረጡ ከተሞች የተገነቡ 309 አነስተኛና መካከለኛ የኢንዱስትሪ ማምረቻ ሼዶች አገልግሎት ሳይሰጡ ቆይተዋል።

እነዚህ ሼዶች በ41 ማዕከላት ላይ የተገነቡ ሲሆን ለኢንዱስትሪ የሚያስፈልጉ መሠረት ልማቶች ስላልተሟላላቸው ከ10 ዓመታት በላይ አገልግሎት ሳይሰጡ መቆየታቸውን ገልፀዋል።

ኮርፖሬሽኑ ሼዶች ለማስተዳደር በ2009 ዓ.ም ከተረከባቸው ወዲህ ያሉባቸውን ችግሮች ለመለየት ጥናት ማድረጉን ጠቅሰዋል።

በተለይ የኤሌክትሪክ ኃይል ፣ የውሃና ሌሎች ችግሮች ሼዶቹ ለታሰበላቸው ዓላማ እንዳይውሉ ማነቆ ሆኖ መቆየቱን አስረድተዋል ።

ኮርፖሬሽኑ እነዚህ ችግሮች በመፍታት  አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የተለያዩ የማሻሻያ ሥራዎችን ማከናወኑን አስረድተዋል።

ሼዶች አገልግሎት ሳይሰጡ ለበርካታ ዓመታት መቀመጣቸው በከተሞች ያለው የሥራ አጥ ጫና ተባብሶ እንዲቀጥል አሉታዊ  ሚና ከመጫወቱም ባለፈ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ልማቱ በሚፈለገው ልክ እንዳያድግ ማድረጉን ገልፀዋል።

አሁን ላይ ሼዶቹ በየአካባቢው በኢንተርፕራይዞች  ለተደራጁ ወጣቶች ተላልፈው እየተሰጡ መሆኑን  ጠቁመዋል ፡፡

በሀዲያ ዞን ሆሳእና ከተማ በሶስት ማዕከላት 25 የማምረቻ ሼዶች እንደሚገኙ የተናገሩት የከተማዋ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰለሞን ግርማ በበኩላቸው ተገንብተው አገልግሎት ሳይሰጡ 14 ዓመታትን አስቆጥረዋል ብለዋል።

ማዕከላቱ ለዓመታት ዝግ ሆነው ከመቆየታቸውም በላይ ለወንጀል ፈፃሚዎች መሸሸጊያ ሆነው መቆየታቸው ጭምር ተናግረዋል።

አደራጅተን ወደ ሥራ የምናስገባቸው ማህበራት በዋናነት የሚያነሱት የመልካም አስተዳደር ጥያቄ የማምረቻ ቦታ ነበር ያሉት አቶ ሰለሞን እነዚህ ሼዶች አገልግሎት መስጠት ባለመቻላቸው ከፍተኛ ወጪ በማውጣት በኪራይ ቤት ለመስራት ተገድደው እንደነበርም ጠቁመዋል ።

በአሁኑ ወቅት ችግሩ በመቀረፉ ማህበራቱን ወደ ማዕከላቱ የማስገባት ሥራ መጀመራቸውን አመልክተዋል።

እንደ ኃላፊው ገለፃ እስከ  አሁን በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የተደራጁ 14 ማህበራት  ማዕከላቱን ተረክበው  ሥራ ጀምረዋል።

የማምረቻ ሼዶቹ አገልግሎት መስጠት የኢንተርፕራይዞችን የቦታ ችግር ከመፍታትም ባለፈ በሥራቸው በርካቶችን ቀጥረው ለማሰራት የተመቹ በመሆናቸው የከተማዋን የሥራ አጥ ጫና ለመቀነስ አይነተኛ ሚና እንደሚጫወት አስታውቀዋል።

በከተማዋ ወደ ማዕከላቱ ገብተው ሥራ ከጀመሩ ማህበራት መካከል የገለቴ ዳቦ ማምረቻ ማህበር ሰብሳቢ ወጣት ተሾመ ከበደ የግለሰብ ቤት ተከራይተው ይሰሩ እንደነበር ነው የገለፀው፡፡

የኪራይ ቤት ካለው ወጪ ባሻገር በነፃነት ለመስራት እንደማይመች የገለፀው ወጣቱ  አሁን ላይ  በሙሉ ልብ እየሰራን ነው ብሏል።

ለጊዜው በቀን እስከ 12 ሺህ ዳቦ በማምረት ለገበያ እያቀረቡ እንደሆነ ገልፆ ተጨማሪ ማሽን በማስመጣት የምርት መጠናቸውን ለማሳደግ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን አስረድቷል።

በሥራቸው 10 ሰራተኞች እንዳሉ የገለፀው ወጣት ተሾመ  ከሥራው መስፋፋት ጋር ተጨማሪ ሰራተኞችን እንደሚቀጥሩ ገልፀዋል።

የሌጋ ህትመትና ጨርቃጨርቅ ሥራ ማህበር ሰብሳቢ ወጣት ወርቅነህ ዱባለ በበኩሉ ከአራት ዓመት በፊት ተደራጅተው ሥራ ሲጀምሩ የማምረቻ ቦታ ስላላገኙ  ከልማት ባንክ ሊያገኙ የሚችሉትን የማሽነሪ ሊዝ ብድር እንዳሳጣቸው አስረድቷል።

አሁን ላይ  ሥራ ስንጀምር የነበረንን ራዕይ ለማሳካት የሚያስችለን ቦታ አግኝተናል ያለው ወጣት ወርቅነህ 9 ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ የማስፋፊያ ሥራ ለማከናወን ማቀዳቸውን አብራርቷል ፡፡

ሥራቸውን በሚያስፋፉበት ወቅትም ተጨማሪ 100 ሰራተኞችን የመቅጠር አቅም እንደሚኖራቸው ነው ያስረዳው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም