የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች የአገሪቱን ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በሙሉ ጊዚያቸው እየሰሩ ነው

60

አዲስ አበባ ሰኔ 15/2012(ኢዜአ) የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ በሙሉ ጊዜያቸው እየሰሩ ካሉ ዲፕሎማቶች በተጻጻሪ በእውቀት ማነስና በአመለካከት ችግር ከቆሙለት አላማ ውጭ የሚንቀሳቀሱትን የማስተካከል ስራ እንደሚሰራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ተናገሩ።

"በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና በአባይ ጉዳይ ከአገሩ ጎን የማይቆም ዲፕሎማት መኖር የለበትም" ብለዋል ሚኒስትሩ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ። 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቃለ መጠይቅ ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ጉዳይ ድርድር በገባችበት ወቅት ማንም ሰው ከአገሩ ጎን መቆም ይጠበቅበታል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች የአገራቸውን ብሄራዊ ጥቅም በማስጠበቅ ረገድ ቀንና ሌት እየሰሩ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና በአባይ ወንዝ ፍትሃዊ አጠቃቀም ዙሪያ ኢትዮጵያ ያላትን አቋም ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ በማሳወቅ ረገድ ሙሉ ጊዜያቸውን ሰጥተው እየሰሩ ነው ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያን ፍትሃዊ አካሄድ የሚቃረኑ ኢፍትሃዊ አካሄዶችን ለተወከሉበት አገርና ለሌሎች አለም አቀፍ አካላት በማስረዳት ከአገራቸው ጎን የቆሙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሁሉም ዲፕሎማቶች ለማለት በሚያስችል ደረጃ ለአገራቸው ብሄራዊ ጥቅም እየሰሩ መሆኑን ገልፀው በአመለካከት ችግርና በእውቀት ማነስ የሚታዩ አንዳንድ ችግሮች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ድርድር በምታደርግበት በዚህ ወቅት ዲፕሎማቶችና ማንኛውም ዜጋ ከአገሩ ጎን መቆም እንዳለበት ያሳሰቡት ሚኒስትሩ የሚታዩ ችግሮችን በመነጋገር እንፈታቸዋለን ብለዋል።

የህዳሴው ግድብና የአባይ ጉዳይ የኢትይጵያ የህልውና ጉዳይ መሆኑን መዘንጋት የለብን ሲሉም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የምታደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ሁሉ በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ተቀባይነት እንዲኖረው በአገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በአንድ ልብ እንዲሰሩም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም