የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ያስገነባው የኮቪድ 19 መመርመሪያ ላብራቶሪ ተመረቀ

49

ፍቼ  ሰኔ 15/2ዐ12 (ኢዜአ) የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የኮረና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በ10 ሚሊዮን ብር ያስገነባው የምርመራ ማእከል ትናንት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት መደረጉን ዩኒቨርሲቲው አስታወቀ ።

የዩኒቨርስቲው ኘሬዝዳንት ዶክተር ገናናው ጐፌ ላብራቶሪው ትናንት በተመረቀበት ወቅት እንደገለፁት ለሰው ጤናና ለሀገር እድገት እንቅፋት የሆነው የኮረና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከልና ለመግታት  ዩኒቨርስቲው የተለያዩ ተግባራትን ያከናውናል፡፡

በተለይም ኮቪድ-19ን ተከትሎ የሚከሰተውን ማህበራዊ መናጋት፣ ሞትና ህመም ለመቀነስ ዩኒቨርስቲው ከማሳወቅና ግንዛቤ ከመፍጠር ባሻገር ህብረተሰቡን በልዩ ልዩ መንገዶች እቅድ አውጥቶ እያገዘ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአሁን የተገነባው የኮሮና ቫይረስ መመርመሪያ ላባራቶሪ በአንድ ቀን 1ሺህ 130 ናሙናዎች የመመርመር አቅም አለው ብለዋል ።

ማእከሉ ከአሁን በፊት ወደ አዲስ አበባ ሲላክ የነበረው የኮሮና ቫይረስ የናሙና ምርመራ በቅርበት በማካሔድ ለተለያዩ የኦሮሚያ ዞኖችና በአካባቢው የሚገኙ የአማራ ክልል አጎራባች ወረዳዎች ተጠቃሚዎች የሚያደርግ ነው ብለዋል ።

በምረቃው ስነ-ስርዓት ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መንግስቱ በቀለ በበኩላቸው የኮሮና ቫይረስ የሚያስከትለውን ቸግር ለማቃለል ቤት ለቤት ማስተማርና ግንዛቤ መፍጠር እንዲሁም መከላከል ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

የምርመራ ማዕከሉ መቋቋም ከእለት ወደ እለት እየጨመረ የመጣውን ወረርሽኝ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ጠቀሜታው የጐላ መሆኑን ጠቅሰው የተጋላጭነት መጠኑን ህብረተሰቡ ሳይዘናጋ የግልና የአካባቢ ንፅህናውን መጠበቅ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የማዕከሉ መገንባት በክልልና በሀገር ደረጃ ያለውን የመመርመር አቅም የሚያሳድግ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

አለም አቀፍ የጥራት ደረጃውን በመጠበቅ የተገነባው ላቦራቶሪው ከኮቪድ 19 በተጨማሪ  ተያያዥነት ባላቸው በሽታዎች ላይ በርካታ ምርምሮችን በማካሄድ ህብረተሰቡ የሳንባ ነቀርሳን፣ ኤች አይ ቪ ኤድስንና ሌሎች በሽታዎች እንዲከላከል ትልቅ እገዛ አለው ያሉት ደግሞ የላብራቶሪው ባለሙያ አቶ በኃይሉ በዛብህ ናቸው፡፡

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ግንባታ ማዕከል ዘርፍ ሚኒስትር አቶ ሞገስ ባልቻን ጨምሮ ከፍተኛ የክልሉ ባለስልጣናት፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም