ኢትዮጵያና ኤርትራ ወደ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋገሩ

71
አዲስ አበባ ሐምሌ 1/ 2010 ጠቅላይ  ሚኒስትር አብይ  አህመድ ኢትዮጵያና ኤርትራ ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገራቸውን አበሰሩ። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ (ዶክተር) ዛሬ በአስመራ ቤተ መንግስት  ልዩ የእራት ግብዣ ላይ  “ኤርትራውያን ወደር የሌለውን ፍቅር ስላሳዩን እናመሰግናለን” በማለት ህዝቡ ላደረገው ፍቅር የተሞላ አቀባበል ያላቸውን አድናቆትና ምስጋና አቅርበዋል። በዚህ ወቅት ነው የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦች በጋራ አልምተው ተጠቃሚ ወደሚሆኑበት ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገራቸውን ያበሰሩት። ዶክተር አብይ አህመድ ከሁለት አስርተ ዓመታት በኋላ አስመራ የገቡና ልዩ አቀባበል የተደረገላቸው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው። የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላኑን ከ20 ዓመት በኋላ ትናንት ጠቅላይ ሚኒስትሩንና የልዑካን ቡድኑን ይዞ በመጓዝ ወደ አዲሱ ምዕራፍ የተደረገው ሽግግር አካል ሆኗል። አየር መንገዱ የዚህ ታሪካዊ ቀን አካል በመሆኑ የተሰማውን ደስታም ባወጣው የፕሬስ መግለጫ ይፋ አድርጓል። “በሁለቱ አገሮች መካከል የነበረው ድንበርና ድልድይ በፍቅር ፈርሷል” በማለት የሁለቱን አገር ህዝቦች ለሃያ ዓመታት አለያይቶ የቆየው የጥላቻ ግንብ መፍረሱን በገለጹበት ንግግራቸው፤ መሪዎቹ የሁለቱ አገሮች አየር መንገዶች ስራ እንዲጀምሩ መስማማታቸውን ነው የተናገሩት። ኢትዮጵያ ወደቦችን እንድትጠቀምና ስራ እንዲጀመር “ተስማምተናል” ሲሉ ነው  የገለጹት። የሰላም አስፈላጊነትን አፅንኦት የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ፤ ኢትዮጵያውያን ወደ ኤርትራ የሚሄዱበት ኤርትራውያን ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ወንድሞቻቸውን የሚጠይቁበት ሁኔታ እንደሚፈጠርም ነው የተናገሩት። ሁለቱም አገሮች ኤምባሲዎቻቸውን ለመክፈትና ህዝቦቻቸው በነጻነት ተንቀሳቅሰው እንዲሰሩ ለማድረግ በውይይታቸው ወቅት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ነው የገለጹት። የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ከፍቅር በላይ መሳሪያ እንደሌለ አጽንኦት ሰጠውታል። በአስመራ የዘነበው የፍቅር ዝናብ ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ብቻ ሳይሆን “ለምስራቅ አፍሪካ የሚተርፍ ነው” ሲሉ ነው በሁለቱ አገሮች መካከል ሰላም መውረድ በቀጣናው ሊፈጥር የሚችለውን መልካም አንደምታ የተናገሩት። የኤርትራው ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ በበኩላቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የሰላማ ጥሪ ከልብ የመነጨና እውነተኛ ሆኖ ማግኘታቸውን ነው የጠቆሙት። ሁለቱ አገሮች ያለፉትን ጊዜያት ወደ ሰላም ለማምጣት ያደረጓቸው ጥረቶች ውጤት እንዳላመጡ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፤ “አሁን ላይ ለስኬት በመደረሱ ምስጋና ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ” በማለት ገልጸውታል። በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የተመራው የልዑካን ቡድን አስመራ ሲገባ ኤርትራውያን የሁለቱን አገሮች ሰንደቅ ዓላማና የዘንባባ ዝንጣፊ በመያዝ በእልልታ አቀባበል አድርገውለታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም