ለጤና ባለሙያዎች የማበረታቻ ስጦታዎች ተበረከተ

54

ደሴ፣ ሰኔ 14/2012 (ኢዜአ) በደቡብ ወሎ ዞን ደሴ ከተማ የሚገኘው "አርሂቡ" ለሰላምና ልማት ማህበር ለቦሩ ሆስፒታል ኮሮና ቫይረስ ህክምና ማዕከል ጤና ባለሙያዎች የማበረታቻ ስጦታዎችን አበረከተ።

በምዕራብ ጎንደር ዞን ለኮሮና መከላከል የሚውል ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተደርጓል።

የ"አርሂቡ" ለሰላምና ለልማት ማህበር ስራአስኪያጅ ወጣት ጣፈጠ ተስፋዬ እንደገለፀው ኮሮናን በመከላከል ህይወታቸውን ሰጥተው ሙያዊ ኃላፊነታቸው እየተወጡ ላሉ የጤና ባለሙያዎች ምስጋና ይገባቸዋል።

ሙያዊ ኃላፊነታቸውን እየተዋጡ ያሉት የጤ ባለሙያዎች ለማበረታታት ከ30 ሺህ ብር በላይ ግምት ያለው መጽሃፍ፣ አራት በግና ሌሎች ድጋፎችንም በቦታው በመገኘት ድጋፉን አበርክተዋል።

በቀጣይ የወረርሽኙን መተላላፊያና መከላከያ መንገዶችን በተለያዩ አካባቢዎች ለህዝቡ በማስተማር በጤና ባለሙያዎች ላይ የሚደርሰውን ጫና ለማቃለል ማህበሩ እንደሚሰራም ወጣቱ ተናግሯል፡

የደቡብ ወሎ ዞን  ኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል ሰብሳቢ አቶ ሰይድ መሃመድ በበኩላቸው ማህበሩ ያደረገው ስጦታ ጤና ባለሙያዎችን ብቻ ሳይሆን እኛንም የሚያነቃቃ ነው ብለዋል፡

የማህበር አባላት  ቫይረሱን ለመከላከል የሚያርጉት ጥረት  የሚበረታታ በመሆኑ ግብረ ኃይሉ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያድርጋላቸውም አስታውቀዋል፡፡

የቦሩ ሆስፒታል ስራአስኪያጅ አቶ ሲሳይ ተበጀ ይህን አስቸጋሪ ወቅት ለማለፍ መተጋገዝ፤ መደማመጥና መተባበር አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

ወጣቶችም አስበው ከጎናቸው በመሆናቸውና ባደረጉት የማበረታቻ ስጦታ መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡

ማህበረሰቡ በጤና ባለሙያዎችና በመንግስት በኩል የሚተላለፉ መልዕክቶችን በመተግበር ራሱንና ቤተሰቡን ከበሽታው በመጠበቅ የጤና ባለሙያዎችን ጫና ማቃለል እንደሚጠበቅባቸውም አመልክተዋል፡፡

"ዛሬ የተበረከተልን ስጦታ የበለጠ እንድንሰራ ያበረታታናል" ያሉት ደግሞ በሆስፒታሉ ጠቅላላ ሐኪምና የኮሮና ህክምና ማዕከሉ ቡድን መሪ ዶክተር ተፈራ ጎበዜ ናቸው፡፡

እንዲህ በመተባበርና መተሳሰብ ጥንቃቄ በማድረግ መከላከል ከተቻለ በሽታው የከፋ ጉዳት ሳያደርስ መቋቋም  እንደሚቻልም ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል በምዕራብ ጎንደር ዞን የአለም ህፃናት ደርጅት ኮሮና ለመከላከል እንዲያግዝ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን የድርጅቱ የመተማ አካባቢ አስተባባሪ አቶ ማሞ ማዘንጊያ ገልጸዋል።

ድጋፉ በለይቶ ማቆያ ገብተው የመቆያ ጊዜያቸውን አጠናቀው ለሚሄዱ ሰዎች ለትራንስፖርትና ለሌሎች ወጪዎች ጭምር የሚውል ነው።

ድርጅቱ በተጨማሪም በአካባቢው የወባ በሽታ ለመከላከል የሚያግዝ የአልጋ አጎበር ለህብረተሰቡ ማሰራጨቱም ተመልክቷል።

በዞኑ የኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ-ኃይል ፀሃፊ ሲስተር ክሽን ወልዴ ድርጅቱ ላደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም