አ.ብ.ቁ.ተ. የዳታ ሴንተርና ኮር ባንኪንግ ሲስተም ማሻሻያ ግንባታ እያካሄደ ነው

166

ባህርዳር፣ ሰኔ 14/2012 (ኢዜአ) የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም /አብቁተ/ የፋይናንስ ዘርፉን ለማዘመን 300 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ የዳታ ሴንተርና ኮር ባንኪንግ ሲስተም ማሻሻያ ቴክኖሎጂ ግንባታ እያካሄደ መሆኑን አስታወቀ።

የተቋሙ ዋና ስራአስፈፃሚ አቶ መኮንን የለውምወሰን ለኢዜአ እንደገለጹት ተቋሙ የሲስተም ማሻሻያውን እያካደ ያለው በፋይናንስ ዘርፉ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመዝለቅ ነው።

የሲስተም ግንባታው በዋናነት ተቋሙ እየሰጠ ያለውን የማይክሮ ፋይናንስ አገልግሎት በቀጣይ ወደ ባንክ ለማሳደግ የያዘውን  ግብ ለማሳካት ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ማሻሻያውም የሞባይልና የኤጀንት ባንኪንግን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ በባንክ ሴክተሩ ተግባራዊ የተደረጉ ቴክኖሎጂዎችን ሁሉ ጥቅም ላይ ለማዋል እንሆነም አስታውቀዋል።

ተገልጋዩን በቀላሉ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንዲሆን ከማድረግ ባለፈ የተቋሙን አሰራርና የአገልግሎት አሰጣጥ በማዘመን ተወዳዳሪ እንዲሆን ያደርጋል ብለዋል።

የማሻሻያ ግንባታው ከተጀመረ ሶስት ወር እንደሆነው ጠቅሰው፤ በቀጣይ ስድስት ወራት ግንባታው ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃም ገልጸዋል።

ተቋሙ ሃዋላን ጨምሮ ሌሎች አገልግሎቶችን የሚሰጡ 500 የማይክሮ ፋይናንስ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችን በመክፈት ለደንበኞቹ አገልግሎቱን ተደራሽ እያደረገ ይገኛል።

አሁን ላይ እየሰጠ ያለውን የማይክሮ ፋይናንስ አገልግሎት ወደ ባንክ ለማሳደግም ለብሄራዊ ባንክ ጥያቄ አቅርቦ ምላሹን እየጠበቀ እንደሆነም ጠቁመዋል።

ተቋሙ ፈቃዱን እንዳገኘም ካሉት የማይክሮ ፋይናንስ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ውስጥ በ60ዎቹ ስራውን በሙከራ ደረጃ ለመጀመር ዝግጁ መሆኑን  አብራርተዋል።

አ.ብ.ቁ.ተ. ከተቋቋመ ሩብ ክፍለ ዘመንን ማስቆጠሩንና  በአሁኑ ወቅትም ከዘጠኝ ሚሊዮን በላይ ተገልጋይ ደንበኞች እንዳሉት ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም