በአዲስ አበባ “ተስፋ” የተባለ የጤና ባለሙያዎች ማህበር የለይቶ ማቆያ ማዕከል ገንብቶ አስረከበ

86

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14 /2012 (ኢዜአ) ተስፋ የጤና ባለሙያዎች ማህበር በአዲስ አበባ ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ጤና ጣቢያ ጋር በመተባበር በ1 ሚሊዮን ብር ያስገነባውን የኮቪድ-19 ምልክት ለታየባቸው የለይቶ ማቆያ ማዕከል አስመረቀ።

በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ጤና ጣቢያ የሚገኙው ተስፋ የጤና ባለሙያዎች ማህበር ከጤና ጣቢያው ጋር በመተባበር ያስገነባውን ማቆያ ማዕከል አስመርቋል።

በምረቃው ላይ የተገኙት የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ስራአስፈፃሚ አቶ ፍቃዱ ካሳሁን የጤና ባለሙያዎች ከተሰለፉበት የሙያ መስክ በተጨማሪ መልካም ተግባር በመፈፀም አርአያነታቸው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

ሁሉም ሰው ባለው እውቀት በመሳተፍ ይህንን አስቸጋሪ ወቅት በጋራ ልናልፈው ይግባልም ነው ያሉት።

የማህበሩ ሰብሳቢ አቶ ቴዎድሮስ ጌታቸው እንዳሉት የለይቶ የማቆያ ማዕከሉን መገንባት ያስፈለገው በጤና ጣቢያው የለይቶ ማቆያ ችግር በመኖሩ ነው።

የኮቪድ-19 ምልክት ታይቶባቸው ወደ ተቋሙ ለሚመጡ ተጠርጣሪዎች የምርመራ ውጤታቸው እስከሚታወቅ የሚቆዩበት መሆኑን ገልጸዋል።

የጤና ባለሙያዎቹ የማቆያ ማዕከሉን በራሳቸው ወጪ ገንብተው በማስረከባቸው ደስተኛ መሆናቸውንም አቶ ቴዎድሮስ ገልጸዋል።

የጤና ባለሙያዎች ከመደበኛ ስራቸው በተጨማሪ በራሳቸው ወጭ ይህን በጎ ተግባር በማድረጋችው የሚያስመሰግን ነው ያሉት ደግሞ የጤና ጣቢያው ሃላፊ አቶ ታምራት አበበ ናቸው።

በእለቱም ማህበሩ በተቋሙ ተመላላሽ ህክምና ለሚያደርጉና ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ታካሚዎችም የማዕድ ማጋራት እና የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አከናውኗል።

ተስፋ የጤና ባለሙያዎች ማህበር ከሶስት አመት በፊት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ጤና ጣቢያ በሚገኙ 22 የጤና ባለሙያዎች የተመሰረት መሆኑ ታውቋል።