የቆዳ ኢንዱስትሪው በአፍሪካ ያለውን ገበያ ለማስፋት እየተሰራ ነው-ኢንስቲትዩቱ

180

አዲስ አበባ፣ ሰኔ14/2012 (ኢዜአ) የቆዳ ኢንዱስትሪው በአፍሪካ ያለውን ገበያ ለማስፋት እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለማሰለፍ የቆዳ ኢንዱስትሪው አስተዋፅኦ እንዳለው ይታወቃል።


ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለሚደረገው መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች መካከልም የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ኢንዱስትሪ ሚና ይጫወታል።

ኢትዮጵያ የቆዳና የቆዳ ውጤት ምርቶቿን ለዓለም ገበያ አቅራቢ ነች።


ምርቶቿን ከምትልክባቸው አገሮች ጣልያን፣ እንግሊዝ፣ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ቻይናና ጃፓን በዋነኝነት ይጠቀሳሉ።

እንዲሁም የሩቅና የመካከለኛ ምሥራቅ አገሮች የኢትዮጵያ ቆዳና ሌጦ ምርቶች መዳረሻ መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።


ይሁንና ለምርቶቹ በአፍሪካ ያለውን ገበያ ግን በሚገባ እንዳልተጠቀመችበት ይገለጻል።


አገቶቱ ዘርፉን ለማሳደግና ተጠቃሚ እንድትሆን መዳረሻዎቿን ወደ አፍሪካና ሌሎች አገሮች ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ቆዳ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ይናገራል።


የኢንስቲትዩቱ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ሰርጄቦ ለኢዜአ እንደገለጹት የቆዳ አምራች ኢንዱስትሪዎች ምርቶችን ወደ አፍሪካ አገሮች ለመላክ ጥረት እየተደረገ ነው።

በዚህም ዘርፉን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለማድረግና የውጭ ምንዛሪ ገቢውን ለማሳደግ ጥናት መደረጉን ገልጸዋል።


በውጭ የሚገኙ ኤምባሲዎችና ቆንስላ ጽህፈት ቤቶችም ለምርቶቹ ገበያ እያፈላለጉ ናቸው ብለዋል።

በዘርፉ የጥሬ ቆዳና ሌጦ ጥራት ችግር፣ የባንኮች ብድር አሰጣጥና የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ዋነኞቹ ችግሮች ይታያሉ። 


እንዲሁም ለቆዳ ፋብሪካዎች ከሚያስፈልገው ኬሚካል በአገር ውስጥ የሚመረተው 10 በመቶ ብቻ መሆኑ  ዘርፉን በሚፈለገው ደረጃ ለማንቀሳቀስ እንዳላስቻለ አስረድተዋል።


በዚህም መንግሥት ችግሮችን ለመፍታትና ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ በጫማ፣ በቆዳ ጓንትና ሌሎች የቆዳ ውጤቶችን የሚያመርቱ 70 ፋብሪካዎች እንደሚገኙና ከ23 ሺህ በላይ ሠራተኞች እንዳሏቸው የኢንስቲትዩቱ መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም