ለ30 ዓመታት ተቋርጦ የነበረውን የጣና በለስ አየር ማረፊያ በአዲስ መልክ እየተሰራ ነው

45

ሰኔ 14/2012( ኢዜአ) ለ30 ዓመታት ተቋርጦ የነበረውን የጣና በለስ አየር ማረፊያ ባለሀብቶችን በማስተባበር በአዲስ መልክ ለማስጀመር እየተሰራ መሆኑ ታውቋል።

በተደረገው እድሳት መሰረትም ነገ የሙከራ በረራ እንደሚደረግ ተጠቁሟል።

የህበረተሰቡን የዘመናት ጥያቄ ለመፍታት ከክልሉ መንግስት ጋር በመነጋገር ለ30 ዓመታት አገልገሎት ሳይሰጥ የቆየውን አየር መንገድ ለማስጀመር እየተከናወነ የሚገኘው በጣና በለስ ስኳር ልማት ፕሮጀክት እና በኢትዮዽያዊው ባለሃብት በአቶ ወርቁ አይተነው አማካኝነት እየተካሄደ እንደሚገኝ የፓዊ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ አሰፋ ተናግረዋል።

የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግና ቀጠናው የተለያዩ ሜጋ ፕሮጀክቶች መገኛ በመሆኑ በተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ለማልማት ለረጅም ጊዜ ተቋርጦ የነበረውን አየር መንገድ የእድሳት ሙሉ ወጭውን በመሸፈን እየሰሩ መሆኑን ባለሀብት አቶ አይተነው ወርቁ ተናግረዋል።

በፓዊ ወረዳ የሚገኘውን የጣና በለስ የአየር መንገድ ዕድሳት ዋና ዓላማ በዞኑ ውስጥ የእርሻ ኢንቨስትመንት ስራዎችን ከማገዝ በተጨማሪ የተለያዩ ባለሃብቶች ወደ ቀጠናው እንዲመጡ ያግዛል ተብሏል።

በቅርብ ጊዜ መደበኛ በረራዎችን በማካሄድ እና የህብረተሰቡን ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ለማድረግ የኢትዮጵያ ሲቭል አቬሽን ባለስልጣን ጉዳዩ ትኩረት በመስጠት መፍትሔ እንዲሰጥ በማሳሰብ የክልሉ መንግስትም የጀመረውን አበረታች ስራ አጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ አቶ ብርሃኑ በወረዳው ህዝብ ስም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የፓዊ ከተማ ነዋሪዎች በበኩላቸው ተቋርጦ የነበረው የአየር በረራ እንዲጀምር በተለያዩ መድረኮች ሲያነሱት የነበረው ጥያቄ ተስፋ ሰጭ እንደሆነ በመግለጽ በረራው ሙሉ በሙሉ ሲጀምር በማህበራዊም ሆነ በኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው ገልጸዋል።

በክልሉ ውስጥ በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ተሳታፊ በመሆን አካባቢውን በማልማት እና ማህበረሰቡን ለማገዝ በሚያደርገው እንቅስቃሴ የክልሉ መንግስት እና የፌድራል መንግስትን ላደረገው መልካም ፍቃድ የደብሊው ኤ ዘይት ማምረቻና ማከፋፈያ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ባለሃብት የሆኑት አቶ ወርቁ አይተነው ምስጋና ማቅረባቸውን ከመተከል ዞን ኮሙዪኒኬሽን መመሪያ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም