በምሥራቅ ወለጋ ዞን በዜግነት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 6 .1 ሚሊዮን ችግኝ የመትከል እንቅስቃሴ ተጀመረ

54

 ነቀምቴ ፣ ሰኔ 13/2012 /ኢዜአ/ በምሥራቅ ወለጋ ዞን በክረምት መርሀ ግብር በዜጎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 6 ነጥብ 1 ሚሊዮን ችግኝ የመትከል እንቅስቃሴ መጀመሩን የዞኑ የሴቶች፣ሕፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ጽህፈት ቤት አስታወቀ ፡፡

መርሀ ግብሩ ትናንት በዞኑ በጉቶ ጊዳ ወረዳ በችግኝ ተከላና በደም ልገሣ ተጀምሯል ፡፡

የዞኑ የሴቶች፣ሕፃናትና ወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሪት እመቤት በየነ እንደገለፁት በዞኑ በሚገኙ 17 ወረዳዎች በዜጎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 6 ነጥብ 1 ሚሊዮን ችግኞችን ይተከላሉ ።

በዕለቱ ከየወረዳዎች እና ከየዞን ሴክተር መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ ሴቶችና ወጣቶች  በመሳተፍ 662 ሺህ ችግኞች ተክለዋል ።

 ከችግኝ ተከላው ጎን ለጎን የደም ልገሣ ፕሮግራም ተካሔዷል ።

በዜግነት የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ የሚከናወኑ 47 የተመረጡና የሕዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሥራዎች ተለይተው ለአስፈፃሚ ወረዳዎች እንዲከፋፈሉ ተደርጓል ።

በክረምት ወራት 200 ሺህ ያህል በጎ ፈቃደኛ ሴቶችና ወጣቶችን በማሳተፍ ከችግኝ ተከላ በተጓዳኝ ደም የመለገሥ፣ አቅመ ደካሞችን የመርዳት፣ አባትና እናት የሌላቸውን ሕፃናት ከጎዳና የማንሳትና የመርዳት፣ የአቅመ ደካሞችን መኖሪያ ቤት የመስራትና የመጠገን ስራዎች እንደሚከናወኑ ወይዘሪት እመቤት አስረድተዋል ።

ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘም በዜጎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ግንዛቤ የመፍጠርና ድጋፍ የማሰባሰብ ሥራዎች ጭምር ለመስራት ዝግጅት መደረጉን ገልፀዋል ።

የምስራቅ ወለጋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ደረጃ አበራ የዜጎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ባስጀመሩበት ወቅት እንደተናገሩት ሴቶችና ወጣቶች ቅንጅት በመፍጠር በደማቅ ሁኔታ የችግኝ ተከላውንና የደም ልገሣ ሥራ መጀመራቸውን አመስግነው ችግኝ መትከል ብቻ ግብ ሊሆን ስለማይችል አስፈላጊውን እንክብካቤ በማድረግ ለፍሬ ለማብቃት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘም በዜጎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ እስከ አሁን የዞኑ ሕዝብ ያደረገው ድጋፍ ተጠናቅሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል ።

የዞኑ ወጣቶች ሊግ ሃላፊ ወጣት ዕድሉ አዱኛ በበኩሉ በዞኑ ከሚገኙ የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ጋር በመተባበር የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለማሳካት ዝግጅት መደረጉን ተናግሯል ።

የዲጋ ወረዳ የሴቶች ሊግ ሃላፊ ወይዘሮ ረጋቱ በቀለ በሰጡት አስተያየት  በአካባቢያቸው የአረንጓዴ አሻራን ለማሳረፍ በችግኝ ተከላው መሳተፋቸውን ገልፀው ለተተከሉ ችግኞች አስፈላጊውን እንክብካቤ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል ።

የጉቶ ጊዳ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ ታሪኬ ዳንኤል በበኩላቸው ደም መለገስ ሕይወትን ማዳን መሆኑን በመገንዘብ ደም በመለገሳቸው ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም