ኤጀንሲው ሦስት ሺህ የንባብ መጻህፍትን ለለይቶ ማቆያና ማከሚያ ማዕከላት ድጋፍ አደረገ

100

ባህርዳር፣ ሰኔ13/2012 ( ኢዜአ)  የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቤተ ጀጽሐፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ በአማራ ክልል የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል ለተዘጋጁ የለይቶ ማቆያና ማከሚያ ማዕከላት ሦስት ሺህ መጻህፍት ድጋፍ ማድረጉን ገለፀ ።

ኤጀንሲው የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ያተኮሩ መጻህፍትን ዛሬ ለክልሉ ኮሮና መከላከል ግብረ ሃይል በባህርዳር ከተማ በመገኘት አስረክቧል።

የኤጀንሲው ተወካይ አቶ አዝዝ ጌትነት ባስተላለፉት መልዕክት በለይቶ ማቆያና በህክምና ማእከላት የሚገቡ ዜጎች ጊዜያቸውን በንባብ በማሳለፍ እውቀትና ክህሎታቸውን እንዲያሳድጉ የሚያስችል ነው።

በቆይታቸውም ንባብን እንደ መዝናኛ በመቁጠር የንባብ ባህላቸውን እንዲያዳብሩና ሊፈጠርባቸው ከሚችል ጭንቀት ራሳቸውን እንዲጠብቁ በማድረግ ፈጥነው እንዲያገግሙ የሚያስችል መሆኑን አስገንዝበዋል።

ድጋፍ የተደረገው ከ900 ሺህ ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው በአገር ውስጥ ምሁራንና ደራሲያን የተፃፉ ሶስት ሺህ መዓህፍት ናቸው ተብሏል ።

መጽሐፍቶቹ  በኢትዮጵያን ታሪክ፣ በፍልስፍና፣ በስነ ልቦና፣ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በሌሎች 77 የተለያዩ አውዶች ዙርያ አውቀት የሚያስጨብጡ መሆናቸውን ተወካዩ ተናግረዋል ።

ቀደም ሲል የውጭና የአገር ውስጥ መጻህፍትን በመግዛት ለአንባቢያን የሚያቀርብ መሆኑን በመጠቆም አሁን ላይ የኮረና ቫይረስ ከተከሰተ ወዲህ ለለይቶ ማቆያና ለህክምና ማዕከላት በነጻ እያቀረበ ይገኛል ብለዋል ።

በአማራ ክልል ለሚገኙ ሁሉም የለይቶ ማቆያና ህክምና ማዕከላት ካደረገው ድጋፍ በተጨማሪ በሀዋሳ፣ መቀሌ፣ አክሱምና አዴግራት ለሚገኙ ማዕከላትም ከ900 ሺህ በላይ መጽሃፍት ድጋፍ ማድረጉን አውስተዋል።

የአማራ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ ምክትል ሃላፊና የግብረ ሃይሉ ጸሃፊ አቶ ታሪኩ በላቸው በበኩላቸው በአማራ ክልል በሚገኙ ማእከላት የገቡ ወገኖች ጊዜአቸውን በመቀመጥና በመተኛት የሚያሳልፉ በመሆናቸው የመጻህፍት እርዳታው ጊዜአቸውን በንባብ እንዲያሳልፉ አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ችግሩን በመረዳት ለህሙማኑ የሚያገለግሉ የንባብ መጽሐፍትን ለማሰባሰብ እንቅስቃሴ እያደረገ ባለበት ወቅት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቤተ መጽሐፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ ድጋፍ በማድረጉ ምስጋና አቅርበዋል።

ህሙማኑ ከጭንቀት ነፃ እንዲሆኑ ከማድረግ ባሻገር የንባብ ባህልን ለማዳበር ያግዛል ብለዋል።

መጽሃፍቱ ከነገ ጀምሮ በክልሉ ውስጥ ለሚገኙ ከ15 በላይ የለይቶ ማቆያና ሌሎች የህክምና ማዕከላት የሚከፋፈል መሆኑን በርክክብ ስነ ስርዓቱ ላይ ተገልጿል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም