ዓለም አቀፍ የስደተኞች ቀን ዛሬ ተከብሯል

187

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13/2012 ( ኢዜአ) ዓለም አቀፍ የስደተኞች ቀን ዛሬ ተከብሮ ውሏል።

ቀኑ በዓለም አቀፍና በኢትዮጵያ በተመሳሳይ ለ17ኛ ጊዜ የተከበረው "እያንዳንዷ ድርጊት ዋጋ አላት" በሚል መሪ ሃሳብ ነው።

የስደተኞች ቀን የሚከበረው በዓለም ስለሚገኙ ስደተኞች ሁኔታ ግንዛቤ በመፍጠር ለስደተኞች ክብር ለመስጠት በማሰብ ነው።

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የዘንድሮው የስደተኞች ቀን በኢንተርኔት በታገዙ ጉባዔዎች መልዕክቶች ታስቦ መዋሉን የዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን /ዩ.ኤን.ኤች.ሲ.አር/ ዕለቱን አስመልክቶ ባወጣው መረጃ እ.አ.አ 2019 ማጠናቀቂያ ድረስ በዓለም 79 ነጥብ 5 ሚሊዮን ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች እንዳሉ አስታውቋል።

ይህም ማለት ከዓለም አጠቃላይ ሕዝብ አንድ በመቶው ከመኖሪያው የተፈናቀለ ነው።

ከ79 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች 45 ነጥብ 7 ሚሊዮኑ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች፤ 26 ሚሊዮን ስደተኞችና በተመሳሳይ እያንዳንዳቸው 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ጥገኝነት ፈላጊዎችና ዜግነት የሌላቸው ናቸው።

እ.አ.አ በ2019 ማጠናቀቂያ 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዜጎች ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው መመለሳቸውን መረጃው ያመለክታል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከመኖሪያቸው ከተፈናቀሉት ውስጥ 40 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ሕጻናት ናቸው።

በአሁኑ ወቅት ሽብርተኝነትን፣ ጦርነትና ጭቆናን ለማምለጥ በየአንድ ደቂቃ ልዩነት አንድ ሰው ከመኖሪያው እንደሚፈናቀል የመንግስታቱ ድርጅት የስደተኞች ኮሚሽን መረጃ ያመላክታል።

ቱርክ፣ ኮሎምቢያ፣ ፓኪስታን፣ ዩጋንዳና ጀርመን ብዙ ስደተኞችን በመቀበል በቀዳሚነት ሲቀመጡ ሶሪያ፣ ቬንዙዌላ፣ አፍጋኒስታን፣ ደቡብ ሱዳንና ማይናማር ብዙ ዜጎች የተሰደዱባቸው አገራት ናቸው።

ሶሪያ 6 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዜጎቿ ለስደት የተዳረጉባት አገር ስትሆን ቱርክ 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ስደተኞችን በመቀበል ከፍተኛውን ድርሻ ይዛለች።

85 በመቶው የዓለም ስደተኞች የሚገኙት በማደግ ላይ በሚገኙ አገራት ውስጥ ነው።

በኢትዮጵያም ከ880 ሺህ በላይ ስደተኞች እንደሚገኙና ከ99 በመቶ በላይ የሚሆኑት የመጡት ከሱዳን፣ ከደቡብ ሱዳን፣ ከኤርትራና ከሶማሊያ መሆናቸውን የኮሚሽኑ መረጃ ያሳያል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዘንድሮውን ዓለም አቀፍ የስደተኞች ቀን አስመልክቶ ባስተላለፈው መልዕክት የኮቪድ-19 ወረርሽኝና በቅርብ ጊዜ ዘረኝነትን በመቃወም የተደረጉ ሰልፎች ሁሉን እኩል አካታች ለሆነ ዓለም መታገል እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል ብሏል።

ሁለቱ ሁነቶች ማንም ሰው ወደኋላ የማይቀርበት ዓለም መፍጠር እንደሚያስፈልግ ያሳዩ እንደሆኑም ገልጿል።

ለውጥ ማምጣት የሁሉም ዜጋ ሃላፊነት እንደሆነና እያንዳንዱ ዜጋም ለውጥ ማምጣት እንደሚችል ድርጅቱ ባስተላለፈው መልዕክት አስታውቋል።

የዘንድሮው የስደተኞች ቀን መሪ ሃሳብ "እያንዳንዱ ድርጊት ዋጋ አለው" ሲባል የእያንዳንዱ ዜጋ ተግባር ሁሉን አቀፍና አካታች ዓለም መፍጠር እንደሚችል አመልክቷል።

በኢትዮጵያም ዓለም አቀፍ የስደተኞች ቀን ትናንትናና ዛሬ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ተከብሯል።

ትናንት ቀኑን አስመልክቶ በስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ቅጥር ግቢ የደም ልገሳ መርሃ ግብር ተከናውኗል።

ዛሬ ደግሞ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች የተለያዩ መልዕክቶችን በማስተላለፍ በስደተኞች መጠለያ ካምፖች የግንዛቤ መፍጠር ስራ በመከወን መከበሩን ከኤጀንሲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

እ.አ.አ በ2000 የተካሄደው 55ኛው የመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ዓለም አቀፍ የስደተኞች ቀን ከአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር 2001 ጀምሮ እንዲከበር በወሰነው መሰረት በየዓመቱ እየተከበረ ነው።

የአውሮፓዊያኑ 2001 ዓ.ም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ኮንቬንሽን የተፈረመበት 50ኛ ዓመት ያስቆጠረበትም ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም